በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡
ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ ማህበራትን ሲደግፍ የቆየው ሌሎችን ለመርዳት ሮጣለሁ ዘመቻ ዘንድሮም ሶስት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ታሳቢ ያደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል፡፡
የ2015 ሶፊ ማልት ቃላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ 10ኪ.ሜ. አካል የሆነው ይህ የገቢ ማሰባሰብ ስራ ታቅዶ የነበረውን የ1.05 ሚሊዮን ብር በታቀደለት መሰረት ከተለያዩ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አሰባስቦ ለ3 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማለትም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለሚገኘው ምዥዥጎ ሎካ፤ የፆታ እኩልነት እና ህጻናት መብት ላይ የሚሰራ ኢማጅን ዋን ዴይ እና የዝናብ አጠር በሆኑና በልማት ተደራሽ ያልነበሩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ትኩረት የሚያደርገው አክሽን ፎር ዴቨሎፕመንት እያንዳንዳቸው የሶስት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ገንዘቡ ከተለያዩ የንግድ ድርጅቶች፣ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቤተሰቦች እና ተሳታፊዎች፣ እንዲሁም በዉጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የዉጭ ዜጎች መሰባሰብ መቻሉ የታወቀ ሲሆን ይህ በጎ አላማ ከገንዘብ ድጎማ ባሻር ስለ ተጠቃሚ ድርጅቶቹ ማንነት እዉቅና መስጠት እና ዘላቂ አጋር ድርጅቶች ጋር የመገናኝት እድሉን ፈጥሩዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 18 አመታት የተለያዩ በጎ አድራጎት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶችን ገቢ በማሰባሰብ እና በማገዝ እንዲሁም የማበረታታት ስራን ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህንንም ስራ በቀጣይነት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡