የሃዋሳ ግማሽ ማራቶን ውድድር ሲጀመር ጀምሮ በአዘጋጅ ቡድን አባልነት ተሳትፌአለሁ፡፡ በተለያዩ አመታት የውድድሩ መንገድ ሲለካ አንዴም ባለ 3 ዙር አንዴም ባለ 2 ዙር ስለሚሆን ሙሉውን ግማሽ ማራቶን ሮጬው አላውቅም፡፡
ባለፈው አመት ግን የውድድሩ መንገድ አንድ ወጥ 21ኪ.ሜ. በመሆኑ መንገዱን ለመለካት ሙሉውን በሳይክል የመጓዝ እድሉ ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ሳይክል መንዳት እና መሮጥ ለየቅል ናቸው፡፡ ውድድሩን ካካሄድን በኋላ በጣም ደስ ደስ የሚሉ አስተያየቶችን ተቀበልን፡፡ በዛም ግን ከመኩራራት ማስተካከያም ካለ ብለን መገምገሚያ ቅጽ ለተሳታፊዎቻችን ልከን ቢሻሻሉ የሚመርጧቸውን ነገሮች ሳይ ግን “ለምን ግማሽ ማራቶኑን አልሮጠውም?” የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡
በስርአት ልምምድ ከሰራሁ ስለቆየሁ ትንሽ ፍርሃት ፍርሃት ቢለኝም ቢያንስ ለተሳታፊዎቻችን ስል መሮጥ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ሃዋሳ ለስራ በሄድንበት አንዱ ቅዳሜ በጠዋት ሹፌራችንን የውድድሩ መነሻ ጋር እንዲያደርሰኝ አደረግኩ እና ሩጫዬን ከመሻው ጀመርኩ፡፡ አልፎኝ ሄዶ 8ኪ.ሜ. አካባቢ ቢጠብቀኝ እያልኩ ስመኝ 4ኪ.ሜ. አካባቢ ስደርስ በጡሩምባው ተሰናብቶኝ ሲነጉድ ፈገግ ብዬ ሸኘሁት፡፡
የውድድሩ መንገድ የመጀመሪየዎቹ 7 ኪ.ሜትሮች ቁልቁለታማ እና በሃዋሳ ሃይቅ ዳር በተሰራ አዲስ አስፋልት ላይ ስለሆነ ከደስታ ብዛት ከአቅም በላይ ላለመፍጠን ራሴን እየተቆጣጠርኩ፤ የሃይቁንም ትንፋሽ በደስታ እየተነፈስኩ ሮጥኩ፡፡
8ኪ.ሜትርን እንዳለፍኩ ግን ወደከተማ የሚያቀና መንገድ እንደሚጠብቀኝ አውቀው ነበር፡፡ ከራሴ ጋር ወሬ ጀምርኩ፤ “የቱጋ ውሃ ልግዛና ልጠጣ?” “ወደ 9ኪ.ሜ. የሚወስደውን መንገድ ልራመደው ወይስ እያቃሰትኩም ቢሆን ልሩጠው?” እያልኩ እንዲሁ እንደምንም በሶምሶማ ወጣሁት እና የታቦር ተራራ ወገብ ደረስኩ፡፡
እዛም ብዙ ሰዎች በተለያየ የስፖርት እንቅስቃሴ ተጠምደው ሳይ ጎሽ የከተማው ነዋሪ ከሳይክል ወደ ሞተር እና ባጃጅ መሻገሩን ማካካሻ ስፖርት ይስራል ማለት ነው እያልኩ ወደ መሃል ከተማ ሩጫዬን ቀጠልኩ፡፡ የውድድሩ አጋማሽ መንገድ ስደርስ ግን ውሃ በጣም አስፈለገኝ፡፡
አንዱ ሱቅ ፊት ቆም ብዬ በያዝኩት ዝርዝር ብር ሩብ ሊትር ውሃ በመግዛት እየቆጠብኩ በመጎንጨትም ፊቴንና ጭንቅላቴን በማርጠብም ሩጫዬን ቀጠልኩ፡፡ ውሃዋን እንደምንም 14ኪ.ሜ. ድረስ ይዣት ሄጄ የመንገድ ጽዳት ላይ የተሰማሩ አንዲት እናት ሳገኝ የሳቸው ቆሻሻ ማስቀመጫ ውስጥ ጥያት ወደ ሃይቁ መንገድ አመራሁ፡፡
የውድድሩ ሶስተኛው ክፍል በሃይቁ ዳር ያለ የኮብል ንጣፍ እና የአፈር መንገድ ሲሆን ልክ ኮብሉ እግሬን ቆንጠር ቆንጠር ሲያረገኝ የአምና ተሳታፊዎችቻችን ለምን “ኮብል በዛው” እንዳሉ ገባኝ፡፡ የውድድሩ በጣም ደስ የሚለው ቦታ ኮብሉ አልቆ የአፈሩ መንገድ ሲጀምር ያለው ነው፡፡ ድካም የሚያስረሳ የዛፎች ጥላ፤ የሃይቅ ትንፋሽ፤ የተለያዩ ትላልቅ ወፎች ሲንጎማለሉ ማየት ሩጡብኝ ሳይሆን ቆም ብላችሁ እዩኝ፤ ተንፍሱኝ፤ ተዝናኑብኝ ይላሉ፡፡ እኔም በፍጥነት እየሮጡ ይሄን የመሰለ ቦታ ለሚያልፉት እያዘንኩ የተወሰነውን በርምጃ የተወሰነውን በሶምሶማ አለፍኩት፡፡
የመጨረሻው ምእራፍ ከ17ኪ.ሜ. በኋላ ያለው ወደ መሃል ከተማ የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ደግሞ የሃዋሳን ከዳገት የጸዳ ከተማ መሆን እንዳመሰግን አድርጎኛል፡፡ የምሬን ጃኬቴን እና ሁለተኛውን ቲሸርቴን ተቀብሎ የሚያስቀምጥልኝ ባገኝ ደስታዬን አልችለውም ነበር፡፡ “ቁም -አቋርጥ-በዚሁ ወደሆቴል ተመለስ” የሚለኝን ድምጽ ባልሰማ እያለፍኩ ሩጫዬን በተወሰነ መልኩ ከአምናው ማስተካከያ ባደርግኩበት መንገድ በመሮጥ በ2:32 ሰአት ስጨርስ የተሰማኝ ደስታ ግን ወደር አልነበረውም፡፡
“በሩጫ የሚዝናና ሰው እድለኛ ነው፤ ሃዋሳ ግማሽ ማራቶንን የሚሮጥ ሰው ደግሞ በጣም በጣም እድለኛ ነው” አስባለኝ፡፡ በተለይ ደግሞ ቀስ እያሉ ለሚሮጡ ሰዎች የሃዋሳ ግማሽ ማራቶን የሚፈጥረው ስሜት ከቃላት በላይ ነው፡፡
ሩጫ የምትውዱ ከሆነ ልምከራችሁ…የሃዋሳ ግማሽ ማራቶንን ሩጡ፤ ተዝናኑ፤ እኔ የተሰማኝን ደስታ ተካፈሉ! ታመሰግኑኛላችሁ ፡)