በትንንሽ አይኖቹ ታላላቆችን አይቶ ያሳየን ፎቶግራፈር
ጂሮ ሞሺዙኪ ይባላል፡፡ በቶኪዮ ተወልዶ መኖሪያውን በፓሪስ ያደረገ ጃፓናዊ ፎቶግራፈር ነው፡፡ በአለም ዙሪያ እየተጓዘ የአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ እና ራግቢ ታላላቅ ውድድሮችን በካሜራው መያዝ ከጀመረ ከ30 ዓመታት በላይ ቆጥሯል፡፡ የስፖርታዊ ትዕይንቶች እና ሌሎችም ስራዎቹን በትልልቅ ሙዚየሞች እና ጋለሪዎች ለህዝብ የሚያሳየው ጂሮ ከኢትዮጵያውያን ታላላቅ አትሌቶች ጋር ልዩ የሚባል ቁርኝት አለው፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ባሳተመው ‘Haile Gebresilassie: Emperor of Long Distance’ (ሀይሌ ገ/ሥላሴ – የረጅም ርቀቱ ንጉሠ ነገሥት) የተሰኘ የአትሌቱን የሩጫ ዘመን ሂደት የሚሳዩ ልዩ ፎቶዎች በብዛት የያዘ መጽሀፍ ካሳተመ ወዲህ ጂሮ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይበልጥ ታዋቂነትን አግኝቷል፡፡ በታላቁ ሩጫ 10 ኪሜ በአዲስ አበባ የባቡር ሀዲድ ማማ ላይ ቆሞ ቁልቁል ካሜራውን ሲያነጣጥር ሺህዎች በርቀት የተመለከቱት ጂሮ ከዱብ ዱብ ጋር በቅርበት ጥቂት አውግቷል፡፡
ዱብ ዱብ፡- ምን ያህል አለም/አህጉር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በካሜራህ አስቀርተህ ይሆን?
ጂሮ፡- አልቆጠርኳቸውም፡፡ በአመት 15 የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ይደረጋሉ፡፡ እኔ ከሌሎቹ ፎቶ ባለሙያዎች በተለየ እስከ 14 ያህሉን እሸፍናለሁ፡፡ ሌሎች ጥቂት የ’Indoor’ እንዲሁም ‘World Challenge GP’ ውድድሮችንም እንደዚሁ ተገኝቼ ፎቶ እወስዳለሁ፡፡ የፓሪስ፣ ለንደን፣ በርሊን፣ ቶክዮ ማራቶኖችን እና የአለም አገር አቋራጭ፣ ዩሮ ኢንዶር ሻምፒዮንሺፕ፣ የአለም ሻምፒዮናዎችም አያመልጡኝም፡፡ ሌሎች አህጉራዊ ሻምፒዮናዎች፣ የወጣቶችና ታዳጊዎች የአለም ሻምፒዮናዎች፣ ኦሊምፒክ፣ የወጣቶች ኦሎምፒክ ላይ ነበርኩ፡፡ ለስድስት ጊዜያት የእግር ኳስ እና የራግቢ አለም ዋንጫዎችን ታድሜያለሁ፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ እና ሌሎች ተመሳሳይ ውድድሮች ላይም ሰርቻለሁ፡፡
ዱብ ዱብ፡- በካሜራህ ካስቀረሃቸው ክስተቶች ልዩው ነበር ስለምትለው አጋጣሚ ንገረን፡-
ጂሮ፡- አዲስ የአለም ሪከርድ ሲመዘገብ ያነሳሁበት ይመስለኛል፡፡ ሀይሌ (ገ/ሥላሴ) በትራክ ላይ እና ሁለት ጊዜ የማራቶን ሪከርድ ሲሰብር እዚያው ነበርኩኝ፡፡ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በተደጋጋሚ ሪከርድ ሲሰብሩ ፎቶአቸው አለኝ፡፡ የአለም ሪከርድ ሲሰበር ማየት ደጋግመህ የምታገኘው እድል አይደለም፡፡
ዱብ ዱብ፡- በካሜራህ ሳታስቀረው ያመለጠህና የሚያስቆጭህ አጋጣሚ ይኖርሀል?
ጂሮ፡- በጣም ብዙ! ሁሉ ነገር የሚሆነው በቅጽበት ነው፡፡ በሰከንድ ክፍልፋይ ጊዜ ውስጥ፡፡ ከስህተትህ መማርህ ነው የሚጠቅምህ፡፡
ዱብ ዱብ፡- የስፖርታዊ ውድድሮች ፈቶ ማንሳት ምን ያህል ፈታኝ ነው?
ጂሮ፡- ብዙም አስቸጋሪ የሚባል አይደለም፡፡ ሙያውን ከወደድከው ትሰራዋለህ፡፡
ዱብ ዱብ፡- የፕሮፌሽናል ስፖርት ፎቶግራፍ ዘርፍ የአትሌቶችን ዝና፣ የኢኮኖሚያዊ አቅም እና ስፖርታዊ ስኬት ለመገንባት አንዱ ቁልፍ መሆኑ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዚህ እድል ምን ያህል ተጠቅመዋል ብለህ ታስባለህ?
ጂሮ፡- ይሄንን ማድረግ አስቸጋሪ አይደለም፡፡ በእነ ሀይሌ፣ ቀነኒሳ፣ ጥሩነሽ ደረጃ ያለህ ጎበዝ አትሌት ከሆንክ አትቸገርም፡፡ የትም ብትሄድ የፎቶ ባለሙያዎች ጥቂት ፎቶዎችን ሊያነሱህ ይወዳሉ፡፡ እና ደግሞ ከሪፖርተሮች ጋር ቆይታ የምታደርግበት በቂ ጊዜ መስጠት ይጠበቅብሀል፡፡