የካቲት 4 ቀን 2014 ዓ.ም.፡- የ2014 ዓ.ም. የሶፊ ማልት የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል እና ስፖርት ቢሮ እንዲሁም በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እና በሌሎች አጋሮች ድጋፍ በመጪው እሁድ የካቲት 6 ቀን ያካሄዳል። የእሁዱ የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን ለ10ኛ ጊዜ የሚደረግ ነው።
በአራት የተለያዩ የውድድር ዘርፎች 2500 ተሳታፊዎች ተሳታፊዎች የሚሮጡበት ይህ ሩጫ የ8ኪ.ሜ፥ የህፃናት እና የ21ኪ.ሜ የጤና ሯጮችና የአትሌቶች ውድድር የ2014 ዓ.ም. የሶፊ ማልት የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን አካል ይሆናሉ።
የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ባለፈው ዓመት ባይካሄድም በ2012 ዓ.ም ውድድሩን ያሸነፈው የግሎባል ስፖርቱ ገብሬ ሮባ ዘንድሮም የድል ክብሩን ለማስጠበቅ ይሮጣል። በ2011 ዓ.ም. አምስተኛ ሆኖ ለጨረሰው ገብሬ የዘንድሮው ውድድር ሶስተኛ ተሳትፎው ነው።
በሐዋሳ ሀይቅ ዙሪያ ከተማውን ከአውሮፕላን ማረፊያው ጋር የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ መጠናቀቁን ተከትሎ የግማሽ ማራቶን ተሳታፊዎች ውድድሩ ባለፉት 9 ዙሮች ከተካሄደባቸው የመሮጫ መንገዶች ለየት ባለውና በሃዋሳ ሃይቅ ዳር እና ሌሎች የከተማው መስህቦች በሆኑት መንገዶች ላይ በአዲስ የመሮጫ ኮርስ የሚደረግ ይሆናል።
የውድድሩ መልዕክት በሆነው “ሀገርዎን ይጎብኙ” የቱሪዝም ሚንስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ለዚህ ውድድር በአጋርነት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር አብሮ ይሰራል፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ታዋቂ ከተሞች እና የቱሪስት መስህቦች የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ያበረታታል።
የግማሽ ማራቶኑ 150 ተሳታፊዎች በሙሉ ከአዲስ አበባ ወደ ውቧ የሀይቅ ዳር ከተማ የሚጓዙ ሯጮች ናቸው።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የብራንድ አጋር እና የውድድሩ የስያሜ ስፖንሰር ሶፊ ማልት በመሮጫ መንገዱ ላይ የሙዚቃ ቦታዎች ያዘጋጀ ሲሆን ተሳታፊዎች ሀይላቸውን የሚያድሱባቸው የሶፊ ማልት መጠጦችም ለተሳታፊዎች ዝግጁ ሆነው ይቆያሉ፡፡ ኃይሌ ሪዞርት ሆቴል ለሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የውድድሩ ይፋዊ ሆቴል ሆኖ ያገለግላል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች ላይ ውሃ በማቅረብ የሚታወቀው አርኪ ውሃም የሃዋሳ ማራቶን ውድድርን ለሚያደምቁ አጋሮቻችን አንዱ ነው፡፡
ማስታወሻ፡ የሐዋሳ ግማሽ ማራቶን የኃይሌ ሪዞርት ሆቴልን በይፋ መከፈትን ለማክበር በግንቦት 2010 ዓ.ም. ተካሄደ። ከውድድሩ አሽናፊዎች መካከል በሪዮ ኦሊምፒክ በ10000 የነሃስ ሜዳልያ ባለድሉ ታምራት ቶላ ይገኝበታል። ውድድሩ ከባህር ወለል በ1700ሜ ከፍታ ላይ ይካሄዳል።
ለተጨማሪ መረጃ hilina@ethiopianrun.org ወይም 0911601710