ጥቅምት 15 ቀን 2014
ኬንያዊቷ እና የሁለት ጊዜ ኦሎምፒክ አሸናፊዋ ፌዝ ኪፕዮገን የ2014 ቶታልኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ እንደምትሆን ታወቀ፡፡ በ1500 ሜትር ውድድር በሪዎ እና ቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊ የሆነችው ኪፕዮገን ህዳር 05 ቀን በሚካሄደው ውድድር ላይ በክብር እንግድነት የምትገኝ ይሆናል፡፡ ባሳለፍነው አመት ማገባደጃ ላይ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምቲክ ውድድር ላይ በማሸነፏ በ1500 ሜትር የአለም ቀዳሚ ራጭ የሚለውን ስያሜን ያገኘችው የ27 አመቷ ኪፕዮገን ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ይህ የመጀመሪያዋ ነው፡፡
ኪፕዮገን ከሃይሌ ገብረስላሴ ጋር በመሆን ከሩጫው በፊት የመጨረሻው አርብ በሃያት ሬጀንሲ በሚካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዲሁም እሁድ በውድድሩ ለት ውድድር ለማስጀመር ትገኛለች፡፡
ኪፕዮገን ወደ ኢትዮጵያ ስለሚኖራት ጉዞ ስትናገር “ ለብዙ አመታት ጎረቤት አገር ኢትዮጵያን መጎብኘት እፈልግ ነበር፡ በኢትዮጵያም በኬንያም ላለን እሯጮች ትልቅ ተፅእኖ በፈጠረው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ወደ ኢትዮጵያ እንድመጣ በመጋበዜ ትልቅ ክብር ይሰማኛል” ስትል “ለብዙ አትሌቶች የመወዳደሪያ መድረክ በመሆን እንዲሁም ሰዎች ጤናማ ያኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ የሚያበረታታውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በማገዜ ደስታ ይሰማኛል” ብላለች፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረም“ የፌዝ ኪፕዮገን መምጣት የውድድሩ መዳረሻ ሳምንት ላይ ጥሩ የሆነ ስሜትን የሚፈጥር ይሆናል: አትሌቲክስን በሚያደንቁ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታዋቂ የሆነችው ፌዝ ውድድርላችን ላይ አብራን ለመሆን በመምጣትዋ ለኛ ክብር ይሰማናል”ብላለች፡፡
በ1500 ሜትር የኬንያን ብሄራዊ ሪከርድ በሞናኮ ባደረገችው ውድድር በ3፡51፡07 አጠናቃ የያዘችው ፌዝ ኪፕዮገን በአለም 1500 ሜትር ሩጫ ሪከርድ ያለተጋሪ ይዛ ትገኛለች፡፡ በ17 አመቷ የአለም ወጣቶች 1500ሜ ውድድርን አሸንፋለች በቀጣይ አመትም የአለም ታዳጊ 1500ሜ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ የመጀመሪያ የኦሎምቲክ አሸናፊነቷን ደግሞ በሪዮ ኦሎምፒክ በ2016 እኤአ አረጋግጣለች፡ በ2017 እኤአ በለንደንም አሸናፊ ነበረች፡፡ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን የነበረውን የቶኪዮ ማራቶን ደግሞ በአሸናፊነት በመጨረስ የኦሎምቲክ ድሏን ደግማዋለች፡፡ በነዚህ ባደረገቻቸው ውድድሮች ላይም እንደ ገንዘቤ ዲባባ እና ሰንበሬ ተፈሪ ያሉ ጠንካራ ተፎካካሪዎችን ተፎካክራለች፡፡
2014 ቶታልኢነርጂስ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመካሄድ 3 ሳምንታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ ውድድሩ በ25ሺ ተሳታፊዎች በሶስት የተለያዩ መነሻ ማእበል የመጀመሪያ ሰአቱን በአዲስ መልክ ከጠዋቱ 2 ሰአት አድርጎ ህዳር 5 ቀን 2014 ይካሄዳል፡፡