በ17ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪ.ሜ. ውድድር ላይ ከ40 ሺህ በላይ የሆኑ ሰዎች ተሳትፈዋል። ሁሉም የሚሳተፉበት የየራሳቸው ምክኒያት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ የተቀራረበ አላማ ይዘው ይሮጣሉ ፣ ዱብዱብ ይላሉ፣ ይራመዳሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ፤ ባለፉት አመታት የገቡበትን ሰዓት ለማሻሻል ከመሮጥ አንስቶ 10ኪ.ሜ. ለመጨረስ እስከመፈለግ ፣ ከቅርብ ጓደኞች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር በስፖርት ለመዝናናት ከመሻት አንስቶ ከድሮ ወዳጆቻቸው ጋር ተገናኝቶ ጥሩ ጊዜ እስከማሳለፍ ፣ ለጤንነት ከመሮጥ እስከ የአትሌቶች የውጤት ውድድር፤ እና ሌሎች በንፅፅር ሊቀመጡ በሚችሉ ነገሮች ሊቀመጥ ይችላል።
ከዚህ ወጣ ባለ መልኩ የተለየ አላማ ይዘው የሚሳተፉም አልጠፉም። ከእነዚህ መሀከል አዲስ እና ሔኖክ ይገኙበታል። የውድድሩ ማስጀመሪያ ጥሩምባ ተነፍቶ ተሳታፊው ሁሉ ሲተም እነርሱ ከፍ ካለ ቦታ ሆነው አረንጓዴውን የህዝብ ጎርፍ በአንክሮ ይከታተላሉ። ይህን ሲያረጉ ባዶ እጃቸውን ሳይሆን ከካሜራ ብሌን ጀርባ አድፍጠው ነበር።
ሁለቱም በየ2 ሳምንቱ በራሳቸው የሚዘጋጅው “Shoot and Run” የተሰኘ ፤ መንገድ ላይ ፎቶግራፍ የማንሳት ፕሮግራማቸውን እያከናወኑ ነው። በዚህ ፕሮግራማቸው በሸገር ጎዳናዎች እና ጉራንጉሮች ውስጥ እየተዘዋወሩ አይናቸው የገባ ቅፀበት በካሜራዎቻቸው ያስቀራሉ። ለህዳር ወር አንደኛው ፕሮግራማቸውን ደሞ የከተማችን መድመቂያ የሆነው ታላቁ ሩጫ የሚካሄድባቸው ጎዳናዎች ላይ ሆኗል።
አዲስ ከዚህ በፊት በታላቁ ሩጫ ላይ በተደጋጋሚ እንደታሰተፈች ትናገራለች። ከዘንድሮው በቀደሙት ጊዜያት ከጓደኞቿ ጋር እየተዝናናች እና ከነሱው ጋር ፎቶ እየተነሳች ከመሮጥ በቀር ሌላው ሰው ላይ ብዙም ታተኩር እንዳልነበር ታስረዳለች። እንዴት ከጠበቀችው በላይ ብዙ ቅፅበቶች በፎቶ እንዳስቀረች እንዲህ ትገልፀዋለች። “እኔ አነሳለሁ ብዬ የጠበኩት ከለርፉል ክራውድ እና አንዳንድ በየመሀሉ የሚደረጉ እንደ ዳንስ ያሉ ክንውኖችን ነበር። በቦታው ግን የገጠመኝ የተለየ ነው። አብዛኛው ሰው ቲሸርቱን በተለያየ መንገድ በማስዋብ ፣ እንደ ጀሪካን ባሉ ቀለል ያሉ ነገሮች ቅርፃቸውን ቀያይሮ በመያዝ ፣ የተለያዩ መልእክት ያላቸውን ፅሁፎች እና ፎቶዎች በቲሸርታቸው ላይ በመለጠፍ ምናምን ድምቅ ብሎ አርፍዷል። ፎቶግራፍ ለመነሳትም ፍቃደኝነታቸውን ሁሉም ተሳታፊዎች በደስታ ሰጥተውናል።”
ሔኖክ “ታላቁ ሩጫ አካባቢ ስደርስ የመጀመሪያዬ ነው።” ብሎ ጀመረልን። “ታላቁ ሩጫን ስንመርጥ ብዙ ለፎቶግራፍ የሚሆኑ ቅፅበቶች እንደሚኖሩ አስበን ነበር። ተሳክቶልናል። ዝግጅቱ ከሩጫም ባሻገር የፌስቲቫል ይዘት አለው። ተሳታፊዎቹ የሚለብሱትን የመወዳደሪያ ቲሸርት ከማሳመር እና የተለያዩ መልእክት ያዘሉ ፅሁፎች እና ስእሎች ከመለጣጠፍ ጀምሮ ፊታቸውን በቀለማት በማስዋብ ለዝግጅቱ ትልቅ ድምቀት ይሰጡታል። ከዚህ የተሻለ ለፎቶግራፍ የሚመች ዝግጅትም ቦታም የለም።” እያለ ይቀጥላል። ሌሎች ከተወዳዳሪዎቹ መሀል በአስራ የሚቆጠሩ የ”shoot and run” ተሳታፊዎች እንደነበሩ እና የእነርሱም ስሜት ተመሳሳይ እንደነበር ጨምሮ ገልጿል።
ከስማርት ፎን መበራከት ጋር ተያይዞ ብዙ ወጣቶችን እየሳበ ያለ ነገር ቢኖር ፎቶግራፍ የማንሳት ዝንባሌ ነው። ወጣቶች በቡድን እና በተናጠል ሆነው በመዟዟር ወይም አካባቢያቸው የሚገኙ የተለያዩ ቅፅበቶችን በካሜራዎቻቸው ያስቀራሉ። ከነዚህ ውስጥ ደሞ ጥቂት የማይባሉት በትርፍ ጊዜያቸው እንደ መዝናኛ አርገው በአማተርነት ሲሰሩት የተቀሩት ቀስ በቀስ ወደ ሙሉ ጊዜ ስራነት ለመቀየር ይፍጨረጨራሉ።
አዲስ እና ሄኖክ ከሁለተኞቹ ወገን እንደሆኑ አስረድተውናል። ፎቶግራፍ ማንሳት በደስታ ጊዜ ከማሳለፊያነት በላይ የሚወዱትን ስራ እየሰሩ እንደ አንድ የገቢ ማስገኛ ፕሮፌሽናል ስራ መሆን እንደሚችል ይገልፃሉ። ሙያው በባህሪው ትምህርት ቤት ገብቶ በመደበኛ ትምህርት ከመማር ይልቅ በስራ የሚዳብር በመሆኑ እንደ ታላቁ ሩጫ ያሉ ትልልቅ ዝግጅቶች ላይ መስራት ትልቅ ልምድ እንደሚያስገኝ በየመሀሉ ያነሳሉ።
ሄኖክ እንደማሳያ የሚያነሳው በዚሁ የግማሽ ቀን ዝግጅት ብቻ ወደ 4ሺህ ፎቶዎችን ማንሳታቸውን ነው። በተለይ እንደ ሩጫ ያለ ፈጣን እንቅስቃሴን ጥራቱን የጠበቀ ፎከስ ያለው ፎቶ ማንሳት ከበድ ያለ ነገር ቢሆንም በድግግሞሽ የሚለመድ በመሆኑ በዝግጅቱ ላይ መሳተፋቸው እንዴት እንደጠቀማቸው አፅንኦት ሰጥቶ ይናገራል።
ከዚህም በላይ ፤ በእለቱ ከተነሱት ፎቶግራፎች መሀል በአዲስ አእምሮ የተነሳ አንድ ለጊዜው ርእስ ያልተሰጠው ፎቶግራፍ አቴንስ በሚገኘው “Black Wall Gallery” ውስጥ “street photography” በተሰኘ አውደ ርእይ ላይ እንዲቀርቡ ከተመረጡት ፎቶዎች ዝርዝር ውስጥ ገብቶ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱም ወጣቶች በፎቶግራፍ ጥበብ መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ አላቸው። በሰፊው በኹነቶች ፎቶግራፍ (Event Photography) ላይ መስራት ይፈልጋሉ። ለዚህም እንደ ታላቁ ሩጫ ባሉ በቅፅበቶች የታጨቁ ዝግጅቶች ላይ በመሳተፍ ክህሎታቸውን እያዳበሩ እና እየተማሩ ይገኛሉ። ሌሎች በተለያየ መልኩ በታላቁ ሩጫ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች የመጡበትን አላማ እያሳኩ ፤ የመጨረሻው ግባቸው ላይ እንኳን ባይደርሱ ከድርጊታቸው እየተማሩ በራሳቸው ላይ እሴት በመጨመር መድረስ ወደሚፈልጉት ቦታ ይሮጣሉ ፣ ዱብ ዱብ ይላሉ ወይም ይራመዳሉ ፤ ቆሞ ግን መቅረት የማይታሰብ ነው። ምክኒያቱም ይህ የታላቁ ሩጫ መንፈስ ነው።