ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚዲያ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
“ባለፉት ሃያ ዓመታት ታላቁ ሩጫ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ ችሏል፧ በዓመት አንዴ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አብሮነት ልባቸውን እንዲሰጡ አድርጓል: በሐይማኖታዊ በዓላት አብረው መሆን ያልቻሉ ዜጎች በታላቁ ሩጫ ተቃቅፈው ይሮጣሉ፤ በብሔረሰባዊ መሰባሰቦች አንድ ላይ መሆን ያልቻሉ ሕዝቦች ታላቁ ሩጫን ጠብቀው ይገናኛሉ::ኃይሌን በታላቁ ሩጫ ስናመሰግነው ዝግጅቱ ለአትሌቲክስ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ መሰባስብን፣ ኢትዮጵያዊ ትስስርን፣ ኢትዮጵያዊ መቀራረብን የምንፈጥርበት በብሔር፣ በቋንቋና በሐይማኖት የማንታጠርበት፣ የሁላችን የሆነ ታላቅ ዝግጅትን ስላስጀመረልን ጭምር ነው::” የኢፊድሪ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በ21ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ቀን ለህዝብ ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ፡፡
ነሃሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም : – የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሀ ብሎ ውድድር ማካሄድ ከጀመረበት 1994 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 18 አመታት ዝግጅቱን ለመላው ሀገሪቱ ተመልካቾች ሲያስተላለፍ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ አሁንም ከ22ተኛው ዙር ጀምሮ የቀጥታ ስርጭቱን በተሻለ ቴክኖሎጂ እና የበርካታ አመታት ልምድ ካላቸው ባለሞያዎች ጋር በመሆን አብሮ ለመስራት ዛሬ ስምምነት ያድሳል፡፡
የዚህ ውድድር በቀጥታ ስርጭት መተላለፍ የሃገሪቷን መልካም ገፅታ ለተቀረው አለም በበጎ መልኩ ለማሳየት ብሎም በአዲስ መልክ የተሰራውን መስቀል አደባባይን በማድመቅ የከተማዋን መልካም ገፅታ ሩጫው በሚካሄድባቸው መንገዶች አስታኮ ለአለም ለማሳየት፤ የአንድነት መንፈስን፤ በሃገር መኩራትን፤ ፍቅርን፤ሰላምን በተለይም ለወጣቱ በተግባር ለማሳየት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር ነው፡፡
በርካታ የውጭ ሃገር ዜጎችን በየአመቱ አሳታፊ የሚያደርገው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ የውድድር ካላንደር የሚያወጣው (AIMS) የሚያወጣውን የውድድር ቀን ተከትሎ ቀኑን ጠብቆ የሚካሄድ ውድድር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ ‘’የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሃገሪቱ ቀደምትና ግዙፍ መገናኛ ብዙሃን እንደመሆኑ መጠን ይህንን አገራዊ ኩነት በቀጥታ ማስተላለፉ ደስታ ይሰማዋል፡፡ ‘’
አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገ/ስላሴ ‘’ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከምሰራቸው ሌሎች ስራዎች ሁሉ አብልጬ የምወደው እና እምኮራበትም ስራ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በጥሩ ጎኗ ለአለም ማሳየት የምንችልበት ለአገራችን ደግሞ አመታዊ የደስታ እና የአብሮነት ቀን መሆን በመቻሉ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ ‘’
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ‘’ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢቢሲ ጋር ለመስራት ስምምነት ላይ በመድረሱ ደስታ ይሰማዋል፡፡ ይህ ውድድር በየአመቱ ሲደረግ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ያላሰለሰ እገዛ ውድድሩ በስኬት እንዲካሄድ ያደርገዋል የዛሬ ውል መፈራረምም አንዱ ማሳያ ነው፡፡‘’ ብለዋል፡፡
የዛሬው ስምምነት ህዳር 11 ለ22ተኛ ጊዜ የሚደረገውን የ2015 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል 10ኪ.ሜ. ብቻ ሳይሆን መጋቢት 4 ቀን 2015 ለ20ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የቅድሚያ ለሴቶች ውድድርንም በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ የሚያበቃ ይሆናል፡፡