መጋቢት 26 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የ2014 አውሮፓ ቀን የህፃናት ሩጫ ውድድር ምዝገባ ዛሬ መጋቢት 26 ቀን ተጀምሯል፡፡
ህፃናት በሰውነታቸው የጎለበቱ እና ንቁ አዕምሮ ያላቸው እንዲሆኑ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል፡፡ ለዚህም የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በአመት ሁለቴ ህዳር እና ሚያዚያ ላይ የህፃናት ሩጫን ላለፉት 13 አመታት አካሂዷል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት ህፃናት ኢትዮጵያውያንና በሃገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ የውጪ ማህበሰብ ልጆችንም የሚያካትት ሲሆን፤ በአራት የተለያዩ የእድሜ ክልሎች (ከ5፣ ከ8፣ ከ11 እና ከ14 በታች) በወንድና በሴት ተከፋፍሎ የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ሩጫው ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት ማዕከል የተለያዩ የህፃናት መዝናኛዎችን፤ ጌም ዞኖችን ጨምሮ ይካሄዳል ፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሜይ 9 ቀን ተከብሮ የሚውለውን የአውሮፓ ህብረት የተቋቋመበትን የሮም ስምምነትን በዓል ተያያዥ አድርጎ በየአመቱ የሚያደረገው የህፃናት ሩጫ እሁድ ሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለ14ተኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ውድድሩ 2000 ተሳታፊዎች ይኖሩታል፡፡