ኢትዮጵያ እና ሩጫ

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

የ19 አመቷ ዮዲት ፓልመር (ስሟ የተቀየረ) በአሜሪካ ሀገር ትኖራለች፡፡  ገና በአራት አመቷ በጉዲፈቻ ከሀገሯ የወጣችው ወጣት አማርኛ ቋንቋ አትናገርም፡፡ አትሰማምም፡፡ ሆኖም በኢንተርኔት ስለ ኢትዮጵያ ለማወቅ ትሞክራለች፡፡ በአጋጣሚዎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ እያነሳች አሜሪካዊያን ጓደኞቿ ስለ ሀገሯ የሚያውቁትን ለመስማት ትፈልጋለች፡፡  ካወራቻቸው በቁጥር የበዙት “ኢትዮጵያውያን ሯጮች ናቸው” ይሏታል፡፡ የሀይሌ ገ/ስላሴን እና ሌሎችንም ታላላቅ አትሌቶች ስም እያስታወሱ ይነግሯታል፡፡ “በዜግነቴ አሜሪካዊት ብሆንም የተወለድኩት ኢትዮጵያ ነው፡፡ ወላጆቼም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የቆዳ ቀለሜም እንደዚያው፡፡ ሆኖም ሩጫ አይሆነኝም፡፡ በምማርበት ኮሌጅ ጓደኞቼ ይቀልዱብኛል፡፡ ‘የማትሮጠው ኢትዮጵያዊት’ እያሉ” ትላለች ዮዲት፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ ዮዲት እና ጓደኞቿ እንደሚያስቧት የሯጮች ሀገር ነች?

ለረጅም አመታት አትሌቲክስን የተከታተለው የስፖርት ጋዜጠኛ ልዑል ታደሰ በዚህ አይስማማም፡፡ “ኢትዮጵያ የታላላቅ ሯጮች ሀገር ነች” ይላል፡፡ “የሯጮች ሀገር ብትሆን ኖሮ ብዙ የተለዩ ማሳያዎች እናገኝ ነበር፡፡ ምን ያህል አትሌቶች አሉን? በአለም ሻምፒዮናዎች እና ኦሊምፒኮች እንዲሁም በሌሎች አህጉራዊ ውድድሮች ለምን ብዙ አዳዲስ ፊቶች አናይም፡፡ ሜዳሊያዎችን ደጋግመው የሚያሸንፉልን አትሌቶች ለምን ውሱን ሆኑ? የላቁ አትሌቶችን የምናገኝበት ኩሬ በማነሱ አይደለም?” ሲል ይሟገታል፡፡

ለረጅም አመታት በአትሌቲክስ አሰልጣኝነት የሰሩት ዶክተር ይልማ በርታ “ኢትዮጵያ የታላላቅ ሯጮች ሀገር ብቻ አይደለችም” ይላሉ፡፡ “ሀገራችን የሯጮች ሀገር ነች” ሲሉ የልዑልን ሀሳብ ይቃረናሉ፡፡ “ታላላቆቹ የተገኙት ከብዙዎቹ መካከል ነው፡፡ በእርግጥ ከተሜነት እና ዘመናዊነት ሲመጣ ከሩጫ ጋር ያለን ዝምድና ቀንሶ ይሆናል፡፡ ሆኖም ህዝባችን አሁንም በአመዛኙ ሯጭ ነው፡፡ በተለይ ቀደም ባለው ጊዜ ሁሉም ሯጭ ነበር፡፡ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት ተራርቀው ነበር፡፡ ልጆች በግብርና ወላጆቻቸውን ሲያግዙ ቆይተው ትምህርት እንዳይረፍድባቸው ይሮጣሉ፡፡ ከትምህርት መልስ ሳይጨልም ወደ መንደራቸው ለመድረስ ይሮጣሉ፡፡ እረኞች ተነጥሎ የሚሮጥ ከብት ለመመለስ ይሮጣሉ፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም ታክሲ እና ሰርቪስ የሚባል ነገር ባልነበረበት ዘመን ይሮጣል፡፡ ወደ ገበያ ለንግድ እና ለሸመታ የወጣው መንደሮችን አቋርጦ ይሄዳል፡፡ ከውጪ ወራሪ ጋር ጦርነት የገጠሙ አባቶቻችን ጦር ግንባር ለመድረስ ከሺህ ኪሎ ሜትሮች በላይ ተጉዘዋል፡፡”

ልዑል የዶክተር ይልማን እይታ ባይቃወምም ሁኔታውን ለይቶ ማየት እንደሚገባ ይናገራል፡፡ “የሯጮች ሀገር ስንል በኑሮ ዘይቤ የተነሳ የሚሮጡትን ማለታችን ነው? ወይስ እንደ ስፖርት ተቀብለውት የሚሮጡትን? በማንኛውም መልኩ የሚሮጠውን ሰው ሁሉ ማለታችን ከሆነ ምናልባትም ከከተማ ውጪ የሚኖሩ ሰዎች በአብዛኛው በዚህ ውስጥ ሊመደቡ ነው፡፡ ይሄም ልማድ ቢሆን እየተሸረሸረ መሆኑን መርሳት አይገባም፡፡ በተለይ የከተማ ነዋሪው የህይወት ዘይቤ በየእለቱ የምንታዘበው ነው፡፡”

“ከቦሌ ወደ ቃሊቲ የሚሄድ ታክሲ ጥበቃ ረጅም ሰዓት የሚሰለፉ ከ100 በላይ ሰዎች ማየት ግር አይልም፡፡ ምክንያታዊ ነው፡፡ ረጅም ሰዓት ተሰልፈው ወደ ታክሲ ከገቡት መካከል ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ወራጅ የሚል ወጣት ስታይ ግን ያስደነግጣል፡፡ ከ8-10ኪ.ሜ. ርቀት 5ብር ከፍሎ በታክሲ የመጣ ሰው ጫፍ ወርዶ ወደ ኮንዶሚኒየም መኖሪያዎች 500ሜትር ከመራመድ ባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ሲጠብቅ ታገኘዋለህ፡፡ ሰዎች እርምጃን ከጠሉ ሩጫን ሊወዱ ይችላሉ?”

ዮዲት ኢትዮጵያውያን ከመሮጥም አልፎ አትሌቲክስ ስፖርትን መመልከት እንደሚያፈቅሩ ታስባለች፡፡ በዩቲዩብ ቪዲዮ አይታለች፡፡ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገሮች ስታድየሞች ውስጥ ባንዲራ ይዘው ሲጨፍሩ አስተውላለች፡፡ ባለፈው ክረምት በለንደን ሙክታር ኢድሪስ እና አልማዝ አያና ሲያሸንፉ ፌስቡክ ላይ የነበረው ስሜት የተለየ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ “በሀገሬ አትሌቲክስ ቀዳሚ ተወዳጅ ስፖርት ነው” ትላለች፡ ነፍስ ካወቀች ወዲህ ኢትዮጵያን ያላየችው ወጣት፡፡

“ጥቂት የማይባሉ ሰዎች እንደዚያ ብለው ያምናሉ፡፡ ሆኖም ትክክል አይመስለኝም” ይላል ልዑል፡፡ በሀገራችን አትሌቲክስ ትኩረት የሚያገኘው በትልልቅ ውድድሮች ወቅት ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ አማራጮች አሉን፡፡ የሀገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮችን በሚካሄድባቸው ቦታዎች ተመልካቾች አሉን? በአዲስ አበባ ስታድየም የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን የሚታደመው ህዝብ የታለ? በጃን ሜዳ ተመልካች አለ? አትሌቲከስ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ብዙ የራዲዮ እና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ከሌሉን ጥያቄ ማንሳት አለብን፡፡ በአትሌቲክስ ላይ ጠለቅ ያለ ቅርበት ያላቸው ጋዜጠኞች ቁጥር ሲያንስ ምን ይነግረናል? የበዛው አድማጭ እና ተመልካች ስለ አትሌቲክስ መስማት የሚመርጠው በአለም ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ ወቅት ብቻ ከሆነስ? ለእነዚህ ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ሳንሰጥ አትሌቲክስ በሀገራችን ተወዳጅ ነው ማለት የተለየ ድፍረት ይጠይቃል፡፡”

ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ከተሜነት በአስገራሚ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን አሀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ2050 ለመጀመሪያ ጊዜ በአህጉሪቱ የከተሜዎቹ ቁጥር በገጠር ከሚኖሩት ሊበልጥ እንደሚችል አለም አቀፍ ተቋማት የሰሯቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሀገራችንም ከ80 በመቶ በላይ ህዝቧን ቀጣሪ ከነበረው ግብርና ይልቅ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ትኩረት መስጠቷ የህዝቦቿ የኑሮ ዘይቤ ይበልጥ ሊለወጥ እንደሚችል ይጠቁማል፡፡ ይህ ለወደፊት የታላላቅ አትሌቶች መገኛ ኩሬዎቻችንን ይበልጥ እያጠበበው ይሆን?

ዶክተር ይልማ አሁንም ተስፋ ይታያቸዋል፡፡ “የተባሉት ችግሮች ሁሉ እያሉ አትሌት ለመሆን የሚለፉት ሰዎች ቁጥር ከፍ ብሏል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር በቡድንም በተናጥል የሚሰለጥኑ ወጣቶች አሉ፡፡ ወደ ጫካዎች ብትሄዱ በየትኛውም ክለብ ያልተያዙ እና ልምምድ የሚሰሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሯጮች ታገኛላችሁ፡፡ እንኳን ቴሌቪዥን ቀርቶ ራዲዮ ይደርሳል ተብሎ በማይገመትበት ቦታ አሁንም ስለ ሀይሌ እና ቀነኒሳ ሰምቼ ሩጫ ጀመርኩ የሚሉ ተስፈኞች አሉ፡፡”

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ