“ስፖርት እወዳለሁ፡፡ በተለይ ለእግር ኳስ ያለኝ ፍቅር ይህ ነው አይባልም፡፡ “ገና ትንሽ ልጅ ሆኜ እንኳን አብረውኝ የሚማሩ ልጆች ኳስ ይዘው ወደ ሜዳ ሲሄዱ እከተላቸዋለሁ፡፡ ልጫወት፡፡ ነገር ግን ተጫውቼ አላውቅም፡፡ ገና ቡድን ሲመራረጡ አንተ ልብስና ደብተር ጠብቅ እባላለሁ፡፡ ሌላም ጊዜ ተስፋ ሳልቆርጥ አብሬያቸው እሄዳለሁ፡፡ እነርሱ ግን ሁልጊዜ ጠባቂ ያደርጉኛል፡፡ እንደማይጠሉኝ አውቃለሁ፡፡ ብዙ ቦታ ለእኔ የማይመች አጋጣሚ ሲፈጠር ከጎኔ ይቆማሉ፡፡ ይደግፉኛል፡፡ እጅግ የምወደውን እግር ኳስ ጨዋታ ግን አይፈቅዱልኝም፡፡ ጭራሽ አያስታውሱኝም፡፡ ከጥበቃው ውጪ ምናልባት ጎል አከራክሯቸው ለምስክርነት ካልሆነ ትዝ አልላቸውም፡፡”
የ27 ዓመቱ ቃልአብ ኪዳነ (ስሙ የተቀየረ) ከልጅነቱ አንስቶ ከአካል ጉዳት ጋር ኖሯል፡፡ ለመራመድ ምርኩዝ/ክራንች መጠቀም የግድ ቢለውም አለመቻል ተሰምቶት አያውቅም፡፡ እርሱ የተቀበለውን ሌሎች አልተቀበሉለትም፡፡ እርሱ መቻሉን ያስባል፡፡ ብዙዎች ግን እድሉን ሳይሰጡት እና ሳይፈትኑት አለመቻሉን ያምናሉ፡፡ ድጋፍ ሲያሻው ከንፈር ይመጡለታል፡፡ በራሱ ሊሰራ ሲነሳ ደግሞ እድል አይሰጡትም፡፡
ይህ በሀገራችን የግለሰቦች ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ የሺህዎች ብቻም አይመስልም፡፡ ምናልባትም የሚሊዮኖች ነው፡፡ በአለማችን ከ650 ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩ ሲገመት ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶዎቹ በኢኮኖሚያቸው ዝቅ ባሉት ሀገሮች ይገኛሉ፡፡ አፍሪካ በአጠቃላይ ከ80-100 ሚሊዮን የአካል ጉዳተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሀገራችን በጥቂቱ ከ10 ሰዎች አንዱ የአካል ጉዳተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡ አካል ጉዳተኞችን ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ብሎም ሌሎች መድረኮች ማራቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የህብረተስብ ክፍሎችን ገሸሽ እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡
ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ስፖርት አንዱ ትልቅ እድል ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሀገራችን እና በሌሎችም ታዳጊ ሀገሮች አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊ የሚያደርጉ ብዙ ውድድሮች አይገኙም፡፡ ቢገኙም በቁጥር እጅግ ውሱን ይሆናሉ፡፡ ታዳጊ ሀገሮች በፓራኦሊምፒክ እና በአለም ፓራአትሌቲክ ሻምፒዮናዎች ያላቸው ተሳትፎ እና ውጤት በንጽጽር አነስተኛ የመሆኑም ምስጢር ከዚህ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንቷ ምህረት ንጉሴ አባሎቻቸው የሆኑ ወጣቶችን በታላቁ ሩጫ ማሳተፋቸው ብዙ ትርጉም እንዳለው ትናገራለች፡፡ “ማህበራችን የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ልጆች እና ወጣቶች ቤታቸው ተቀምጠው ለተጨማሪ የአእምሮ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ወጣ ብለው ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ ስልጠና ማግኘት የማይችሉትን ደግሞ በተለያየ መልኩ ማህበራዊ ህይወታቸው እንዲስተካከል ልናግዛቸው እንጥራለን፡፡ ታላቁ ሩጫ ይሄንን እድል ይሰጠናል” ትላለች፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከ1996 ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት በውድድሮቹ የአካል ጉዳተኞችን አሳታፊ ፕሮግራም አሰናድቷል፡፡ በህጻንቱ ውድድር የአካል ጉዳት እና አእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው ልጆች ቦታ አላቸው፡፡ በተለይ የህዳሩ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ከመጀመሩ ከደቂቃዎች አስቀድሞ በተሸከርካሪ ወንበር የሚንቀሳቀሱ ከ30-35 የሚደርሱ የአካል ጉዳተኞች በመስቀል አደባባይ /Mobility Race/ የሚሰኘውን ውድድር ያደርጋሉ፡፡ ይህ ውድድር በወንዶችና በሴቶች ተከፍሎ ሁለት ጊዜ የሚደረግ ሲሆን ከ200 – 500 ሜትር በሚሸፍነው ውድድር አሸናፊ የሚሆኑት ተሳታፊዎች በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ስነ ስርዓት ሽልማት ይቀበላሉ፡፡ በዚህ ውድድር የተሳተፉና ሌሎችም ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት የመጡ ተሳታፊዎች በተመሳሳይ ካናቴራ ከሌሎች ሺህዎች ጋር የ10 ኪሎ ሜትሩን ውድድር ይቀላቀላሉ፡፡
በሀገራችን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞችን ቀን ምክንያት አድርገው ከሚዘጋጁ የስፖርት ፌስቲቫሎች ባለፈ ሁሉንም የአካል ጉዳተኛ የሚያሳትፉ ብዙ ውድድሮች አይገኙም፡፡ እንደ ቃልአብ ያሉ ወጣቶች በየአመቱ የታላቁ ሩጫን በናፍቆት የሚጠብቁበት አንዱ ምክንያት ይሄው እድል ማጣት ነው፡፡
በአትሌቲክስ በአለም ላይ ስኬታማ የሚባሉ አትሌቶችን ያፈራችው ኢትዮጵያ በፓራኦሊምፒክ፣ በአለም ፓራአትሌቲክ ሻምፒዮና እና በሌሎችም የአካል ጉዳተኞች በሚወዳደሩባቸው መድረኮች የተሻለ ተሳትፎ እና ውጤት ማግኘት ትችላለች፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እና ጥሩነሽ ዲባባ የማሰልጠኛ ማዕከል የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተማር ጀምረዋል፡፡ ለጊዜው በእጆቻቸው እና አይኖቻቸው ላይ መለስተኛ ጉዳት ያለባቸውን ተማሪዎች በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡
“ልጆቹ እድል ከሰጠሀቸው ያስገርሙሀል፡፡ ውድድር ሲካሄድ በቦሌ ክፍለ ከተማ የእኛ ቢሮ የሚገኝበት ወረዳ ተደጋጋሚ ዋንጫ እና ሜዳሊያ ያሸንፋል፡፡ ምክንያቱ ሌላ አይደለም፡፡ ቅርብ ያሉት ልጆች ወደ እኛ እየመጡ የመጫወትና የመለማመድ አድል ስለሚያገኙ ብቻ የተሻለ ውጤት ሲያመጡ አይተናል” ትላለች ምህረት፡፡ “መወዳደር መቻል ጥሩ ቢሆንም ይሄ ለብዙዎች የሚደርስ አድል አይደለም፡፡ ብዙዎችን የሚያሳትፍ ብዙ ውድድር ያስፈልገናል፡፡ እንደ ታላቁ ሩጫ ባለ መድረክ ልጆቻችን መወዳደር ብቻ ሳይሆን ይዝናናሉ፡፡ እኩልነት ይሰማቸዋል፡፡ ሌሎች ጓደኞችም ያፈራሉ፡፡ ከዚህ ሌላ ለተቀረው ህብረተሰብ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ በሩጫው መሳተፍ፤ መወዳደር፤ መስራት እና ማሸነፍ እንደሚችሉ ይናገሩበታል፡፡”
“ከዚህ በኋላ ስፖርተኛ መሆን እንደማልችል አውቀዋለሁ፡፡ ሆኖም በውድድሮች ላይ መሳተፍ እፈልጋለሁ፡፡ ከአምስት አመት በፊት በታላቁ ሩጫ ለመሳተፍ ካናቴራ ሳገኝ በጣም ተደስቼ ነበር፡፡ 10ኪሎ ሜትሩን ከሌሎች ሺህዎች ጋር እየተደሰትኩ ጨረስኩ፡፡ ከሁሉም የመጨረሻው ሰው ሆኜ እንደማጠናቅቅ አስቤ ነበር፡፡ ሜዳሊያዬን ስወስድ ዞር ብዬ አየሁ፡፡ ሌሎች ሺህዎች ከኋላዬ ነበሩ” ይላል ቃልአብ፡፡