አንዱዓምላክ በልሁ

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

“ለታላቁ ሩጫ እየተዘጋጀሁ ነው”

ልጁ ስመ ብዙ ነው፡፡ ወንድሞቹ “ሀብታሙ” ይሉታል፡፡ እናት እና አባቱ በጉራጊኛ “ካብቱ” (ሀብታሙ) ብለው ይጠሩታል፡፡ አያቱ ደግሞ ከህጻንነቱ አንስቶ “ስራህ ብዙ” ይሉታል፡፡ “ተናጋሪ እና ቀልቃላ ቢጤ ስለነበርኩ መሰለኝ” ይላል የስሙ ባለቤት፡፡ የ21 አመቱ ወጣት ባለፉት አራት ዓመታት ብዙ ተለውጧል፡፡ በ2005 ዓ.ም. የስምንተኛ ክፍል ፈተናውን ከወሰደ በኋላ ሁሉም ነገር በፍጥነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንደ መጠሪያ ስሙ ሁሉ ታሪኩም ሌላ ሆኗል፡፡

በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የተወለደው አትሌት በ2005 የትምህርት ቤቶች ውድድር አይን ውስጥ ከገባ በኋላ በወረዳው በሚገኝ የአትሌቲክስ ፕሮጀክት ታቅፏል፡፡ በሁለት አመት የፕሮጀክት ቆይታው የቀለም ትምህርቱን ጎን ለጎን ተከታትሎ ጨርሷል፡፡ የማትሪክ ውጤቱ ጥሩ የሚባል ቢሆንም ወደ ሁለተኛ ደረጃ መሰናዶ ትምህርት ከመግባት እና አትሌቲክሱ ላይ ከማተኮር አንዱን መምረጥ እንዳለበት ወሰነ፡፡ አትሌቲክስን መረጠ፡፡

በ2009 በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ሻምፒዮኑ እና በለንደን የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሀገሩን ከወከለው አንዷዓምላክ በልሁ ጋር ዱብ ዱብ አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡ 

ዱብ ዱብ፡- ወላጆችህ፣ ወንድሞችህ እና አያትህ የሚጠሩህ በተለየ ስም ከሆነ አንዱዓምላክ ብሎ ስም ያወጣልህ ማነው?

አንዱዓምላክ፡- እኔ ራሴ ነኝ ያወጣሁት፡፡

ዱብ ዱብ፡- እንዴት እና ለምን ራስህን ‘አንዱዓምላክ’ አልክ?

አንዱዓምላክ፡- ፊቴን ወደ ሩጫ እንዳዞርኩ ሳውቅ ለፈጣሪ ክብር መስጠት ፈለግሁ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ሯጭ ባትሆን ኖሮ የት እናገኝህ ነበር?

አንዱዓምላክ፡- ነጋዴ እሆን ነበር፡፡ ያው ጉራጌ እንደምታውቀው (ሳቅ…)፡፡ ምናልባትም ደግሞ ትምህርቴን እቀጥል ነበር፡፡ ግን ወደ ንግዱ አዘነብል የነበረ ይመስለኛል፡፡

ዱብ ዱብ፡- የወጣህበት ቤተሰብህ ሠፊ የሚባል ነው? አንተስ ስንተኛ ልጅ ነህ?

አንዱዓምላክ፡- ልጆች አምስት ነን፡፡ ደግሞ ሁላችንም ወንዶች ነን፡፡ እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ እንግዲህ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ታላላቆችህ በምን ስራ የተሰማሩ ናቸው?

አንዱዓምላክ፡- በንግድ ዘርፍ ውስጥ ናቸው፡፡

ዱብ ዱብ፡- በ2009 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ሩጫ ሙክታር ኢድሪስን በመጨረሻዎቹ ሜትሮች አሸነፍከው፡፡ ሙክታር ውድድሩን እንዳሸነፈ እርግጠኛ ይመስል ነበር፡፡

አንዱዓምላክ፡- አዎ… ሙክታርን አልጠበኩትም ነበር፡፡ የእኔ ሀሳብ 100 ሜትር ሲቀረው ለመውጣት ነበር፡፡ እርሱ 200 ሜትር ሲቀር ለካ ከኋላ መምጣት ጀምሯል፡፡ ከዛ ሁላችንም ሙክታር፣ አባዲ (ሀዲስ) እና ሞገስ (ጥዑማይ) እና እኔ ተከታትለን ኩርባውን ጨረስን፡፡ 100 ሜትር ሲቀረን ልወጣ ስዘጋጅ ነው መክታርን ያየሁት፡፡ ያኔ በድንጋጤ ነው ፍጥነቴን የጨመርኩት፡፡ ሙክታር የመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ ምን እንዳሰበ አላውቅም መሙን ለቅቆ ሶስተኛው ላይ ገባ፡፡ ይሄኔ እኔ በነበርኩበት መስመር ጨረስኩ፡፡ አሸነፍኩ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ምን አይነት ውድድር ይበልጥ ምቹ ይሆንልሀል?

አንዱዓምላክ፡- ፔስ ሲከርር (ወጥ  በሆነ ፍጥነት የሚሮጥበት ሲሆን) ይበልጥ ይመቸኛል፡፡ የዙሩ ፍጥነት ፈጠን ቀዝቀዝ ሲል ብዙም አይሆነኝም፡፡

ዱብ ዱብ፡- ሩጫ ልትተው ያሰብክበት ጊዜ ነበር?

አንዱዓምላክ፡- አዎ፡፡ ወንድሞቼ ትክክለኛውን ውሳኔ ስለመወሰኔ እርግጠኛ ስላልነበሩ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ሰልችቶት ይተወዋል የሚል ሀሳብ ስለነበራቸው ብዙ ድጋፍ የሚያረግልኝ አልነበረም፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ በግል ስሰራ የትጥቅ አለመሟላትና ሌሎችም ከባድ ነገሮች ማለፍ ነበረብኝ፡፡ በመሀል ልተወው አስቤ የነበረው ያን ጊዜ ነው፡፡ ክለብ ባላገኝ ኖሮ ፈተናውን መቋቋም አልችልም ነበር፡፡

ዱብ ዱብ፡- አሁን የደረስክበትን ደረጃ ሲያዩት ምን ይሉሀል?

አንዱዓምላክ፡- ታሪክ ነው የሚሆንባቸው፡፡ የሆነውን ማመን ይቸገራሉ፡፡ አሁን በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡

ዱብ ዱብ፡- በታላቁ ሩጫ የመሳተፍ እድል ነበረህ?

አንዱዓምላክ፡- አልተሳተፍኩም፡፡ ለዘንድሮው እየተዘጋጀሁ ነው፡፡

ዱብ ዱብ፡- በጣም እናመሰግናለን አንዱዓምላክ!

አንዱዓምላክ፡- አመሰግናለሁ!

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ