ዱብዱብ፡- አርቲስት አለማየሁ ጥሩ የሚባል ቁመና ላይ ትገኛለህ፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ታደርጋለህ?
አለማየሁ፡- አዎ፡፡ ሌላው ቀርቶ ወደ መድረክ ከመውጣታችን በፊት የተለያዩ ስፖርቶችን እንሰራለን፡፡ ሁለት ሰዓታት ያህል ጊዜ የሚወስዱ ቴአትሮችን በብቃት ለመወጣት የአካል ብቃት ይጠይቃል፡፡ ቀደም ሲል ጂምናዚየም ውስጥ ስፖርት እሰራ ነበር፡፡ በኋላ ግን የወገብ ህመም ገጠመኝና ዎክ /እርምጃ/ እና ሶምሶማ አደርጋለሁ፡፡ ከሁሉ በፊት ግን ዮጋ ስፖርትም አዘወትር ነበር፡፡
ዱብዱብ፡- ስፖርት ማዘውተር ለትወና ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
አለማየሁ፡-የመድረክ ተዋናይ ስትሆን ለሚመጡ ገጸ-ባህርያት ምቹ ሆነህ መጠበቅ አለብህ፡፡ ምክንያቱም በትወና የአእምሮህ እና አካልህ ጥምረት ያስፈልጋል፡፡
ዱብዱብ፡-አሌክስ የሚያረጅ አይነት አይደለም፡፡ ሽማግሌ ሆኖ ሲሰራ ማየት ሲያምረን ሊቀር ነው ብለው የሚቀልዱ ሰዎች ሰምቻለሁ…
አለማየሁ፡- (ረጅም ሳቅ) ከ10 ዓመት በፊት ሽማግሌ ሆኜ አንቲገንን ሰርቻለሁ፡፡ የሚከብደው ከላይ ወደ ታች ነው፡፡ ከታች ወደ ላይ ችግር የለውም፡፡ በሜካፕም ታግዞ ይመጣል፡፡
ዱብዱብ፡- ከተጫወትካቸው ገጸ-ባህርያት መካከል የአካል ብቃትህን በጣም የፈተነ የምታስታውሰው
አለማየሁ፡-አሉ አሉ…
ዱብዱብ፡- ለምሳሌ?
አለማየሁ፡-በጣም ቆይቷል፡፡ እስረኛው ንጉስ ፈታኝ ነበር፡፡ የንጉሡ አጫዋች ሆኜ ነበር የሰራሁት፡፡ ድምጼ ተለውጧል፡፡ አካሌም እንደዚያው፡፡ ገጸ-ባህሪው አካላዊ ሁኔታው ከወገቡ ጎንበስ ብሎ አግሮቹ በጥቂቱ የታጠፉ እና በጣቶቹ ጠርዝ እየረገጠ የሚራመድ ሰው ሆኜ ነበር የሰራሁት፡፡ ያንን ለመስራት የግድ ሰውነትህ መታዘዝ አለበት፡፡ ተመሳሳይ መሆን ስላለበት እስከ መጨረሻው ከዚያ አካላዊ ሁኔታ ውጪ መሆን አትችልም፡፡ ከተፈጥሯዊ ሁኔታህ ውጪ አነሰ ቢባል ለ15 ደቂቃዎች በዚያ ሁኔታ ትቆያለህ፡፡ ጥቂት ከተለወጥክ ገጸ-ባህሪው ይበላሻል፡፡ በዚያ መልኩ ቆይተህ ከቴአትሩ በኋላ ተጽዕኖ ያደርግብሀል፡፡
አንቲገን ላይ እንደዚሁ ንጉስ ክሬዎንን ሆኜ ነበር የሰራሁት፡፡ እድሜው የገፋ እና ጥቂት ጎንበስ ያለ ንጉስ አቋም ነበረው፡፡ በዚያ አቋም የንጉሱን የድምጹን ሞገስ ታመጣለህ፤ ቃለ-ተውኔትህን ታስታውሳለህ፤ ስሜትህን ትቆጣጠራለህ፡፡ ይህን ለመስራት መጀመሪያ ሰውነትህን አሳስበህ ለየትኛውም አካላዊ ለውጥ ምቹ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ቴአትር በተፈጥሯዊ አቋምህ ስትሰራው እንኳን አድካሚ ነው፡፡ ተዋናይነት የአካል ብቃት ይጠይቃል፡፡
ዱብዱብ፡- በታላቁ ሩጫ ውድድር ተሳትፈህ ታውቃለህ?
አለማየሁ፡- አዎ አምስት ጊዜ ያህል ሮጫለሁ፡፡ ከባለቤቴ ጋር ሁለት ጊዜ ያህል ሮጫለሁ፡፡ የመጀመሪያው ታላቁ ሩጫም ላይ ነበርኩበት፡፡ ገና ፕሮሞት ሲደረግ በጉጉት ነበር የጠበቅነው፡፡ መስቀል አደባባይ ኤግዚቢሽን መግቢያው ላይ ልምምድ እንሰራ ነበር፡፡ 10ኪ.ሜ. በጣም ከባድ መስሎን ነበር፡፡ የሆነ የማይቻል በቃሬዛ የምንወጣ ነበር የመሰለን፡፡ በቡድን ነበር ልምምዱ የተሰራው፡፡ ብዙ ነበርን… ሱራፌል ወንድሙ፤ ብርሀኔ ንጉሴ፤ ተስፋዬ ገ/ሃና… በርከት ብለን ነው፡፡ የዝግጅት መመሪያውን በሬዲዮ እየሰማን፤ እየተለማመድን፤ ፍል ውሃ እየገባን ምናምን ተዘጋጀን፡፡ እኔ ጂም እሰራ ስለነበር በጥሩ ሰዓት ነው የገባሁት፡፡ በቀጣዩ እንዲያውም ሳልፈልግ የራሴን ሪከርድ እንዳሻሽል አደረጉኝ፡፡ ስሮጥ ሰዎች ሲያዩኝ ‘እንዴ.. እስካሁን እዚህ ነህ?’ ሲሉኝ ፍጥነት ስጨምር ከፊት ያሉትም ‘አሌክስ ሞተሃል’ ሲሉኝ ስሮጥ ባለቤቴን ትቻት ገብቻለሁ (ሳቅ)፡፡
ዱብዱብ፡- በሶስት ሰዓት ውስጥ ፉት አደረግካት? (ሳቅ)
አለማየሁ፡- ( ረጅም ሳቅ )… ተው ተው ከአንድ ሰዓት በታች ነው የገባሁት፡፡
ዱብዱብ፡- ከሀገራችን አትሌቶች አብልጠህ የምትወደው ማንን ነው?
አለማየሁ፡-ሀይሌ፡፡ የተለየ ብቃት ነበረው፡፡ በተለይ ያቺ ፖል ቴርጋትን የቀደመባት ቅጽበት ደግሜ ባየኋት ጊዜ ሁሉ ታስደንቀኛለች፡፡
ዱብዱብ፡-ያን ውድድሩን ያየህበትን ቦታ ታስታውሰዋለህ?
አለማየሁ፡-ሜጋ ኪነጥበባት እንሰራ ስለነበር ወደዚያ ቀረብ ያለ የጓደኛችን ኪራይ ቤት ነበር ያየነው፡፡ እዚያ ተሰብስበን አያየን የመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ ሀይሌ ቴርጋትን ሲቀድመው ቅልልል..ጥ አድርገን እንጮህልሀለን፡፡ አከራዮቹ ሩጫ መኖሩን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ ግቢው ውስጥ አንዲት ውሻ ነበረች ማንዲ የምትባል፡፡ ተኩስ ከሰማች ምናምን የምትገባበት ነው የሚጠፋት፡፡ እኛ ስንጮህ ማንዲም የውሻ የማይመስል ጩኸቷን አቀለጠችው፡፡ ጊቢው ቀውጢ ሆነ፡፡ ይሄ ጩኸት በመላው ኢትዮጵያ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በኋላም የጮህነው አይመስለኝ… በስፖርት፡፡
ዱብዱብ፡- ከልጆችህ ወደ ስፖርቱ ያዘነበለ አለ?
አለማየሁ፡-ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ሶስተኛዋ ሴት ነች፡፡ መሀከለኛው (አሜን አለማየሁ) ዘጠኝ አመቱ ነው፡፡ እግር ኳስ ይወዳል፡፡ የአውሮፓ ኳስ መረጃ በዝርዝር ማወቁ ይገርመኛል፡፡ ሲጫወትም ጎበዝ ነው፡፡ ወደ ፊት ተጫዋች እንደሚሆን ያስባል፡፡ ኢትዮጵያ ለአለም ዋንጫ አለመብቃቷን እያነሳ በእርሱ ጊዜ እንደምትደርስ ይናገራል፡፡