አሠፋ መዝገቡ – አትሌቱ!

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

ይህ ስም በኢትዮጵያ ታዋቂ ነው – አሠፋ መዝገቡ፡፡ ከ25 ዓመት በታች የሆኑትን ወጣቶች “አሠፋ መዝገቡ” ማነው? ብላችሁ ጠይቋቸው፡፡ ሳያመነቱ “ትራፊክ ነዋ!” ይሏችኋል፡፡ ከፍ ያሉትን ጠይቋቸው፡፡ “አሠፋ መዝገቡ” ማነው? እነዚህኞቹ ምናልባትም ጥያቄያችሁን በጥያቄ ይመልሱላችኋል፡፡ “አሠፋ መዝገቡ አትሌቱ? ወይስ ትራፊኩ?” አሁን ዱብ ዱብ እንግዳ አድርጋ የምታቀርብላችሁ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ባለቤቱ እና የሌሎች በርካታ ሜዳሊያዎች አሸናፊው አትሌቱ አሠፋ መዝገቡ ነው፡፡ ብዙዎች አሁንም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የቡድን ስራ እና መስዋዕትነት ምሳሌ ያደርጉታል፡፡ የሀይሌ ገብረስላሴን የስኬት ዘመናት የሚያስታውሱ ሁሉ የአሠፋን ጠንካራ አትሌትነት ያወሳሉ፡፡ ለአቴንስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ሆቴል ከገባ በኋላ ከገጠመው የጉልበት ጉዳቱ ማገገም ባለመቻሉ ገና በጊዜ ሩጫን ተሰናበተ፡፡ በ2004 ዓ.ም. ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሳውዝ ካሮላይና በሚገኝ ኮሌጅ አትሌቶችን ለማሰልጠን የሄደው አሠፋ ለአራት አመታት የስፖርት አስተዳደር ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ ከአሠፋ ጋር የደረግነው አጭር ቆይታ ይሄው…

ዱብ ዱብ፡- አሁን በምን ስራ ላይ ትገኛለህ?

አሠፋ፡- ግሎባል ስፖርት ኮሚዩኒኬሽን ከሚባል ተቋም ጋር በአሰልጣኝነት እሰራለሁ፡፡ ለረጅም አመታት የእኔ፤ ሀይሌ እና ቀነኒሳ በቀለ እንዲሁም አሁን የአልማዝ አያና ማናጀር የሆኑት ጆስ ኸርመንስ ጋር አብረን እንሰራለን፡፡

ዱብ ዱብ፡- ትምህርትህን አጠናቅቀህ ስትመለስ ከእነ ሀይሌ ጋር ወደ ፌዴሬሽን አመራርነት እንደምትመጣ ተጠብቀህ ነበር፡፡ ወዴት ሸሸህ? 

አሠፋ፡- …(ረጅም ሳቅ)፡፡ ሽሽት አይደለም፡፡ እንደመጣሁ ሀይሌም ገብሬም (ገ/እግዚአብሔር ገ/ማሪያም) እንድቀላቀላቸው ጠይቀውኝ ነበር፡፡ በእርግጥ ወደዚያ መግባቴ አይቀርም፡፡ ለጊዜው ጥቂት የስራ ልምድ ይኑረኝ ጥቂት ታገሱኝሰ ብያቸው ነበር፡፡ እንጂ ሽሽት አይደለም…

ዱብ ዱብ፡- አንተ ከሩጫው መድረክ ራቅ ስትል ስምህ ከሬዲዮ አልራቀም፡፡ ኢንስፔክተር አሠፋ መዝገቡ የሚለው ስም ታዋቂ ነው፡፡ የስማችሁ ሞክሼነት ምን ገጠመህ?  

አሠፋ፡- …(ሳቅ) ጥቂት ቀደም ያለው ትውልድ ነው የሚያውቀኝ፡፡ ያሁኖቹ የሚያውቁት ኢንስፔክተሩን ነው፡፡ በእርግጥ በየእለቱ ጠዋት ሬዲዮ ላይ እንደመሰማቱ አሁን እርሱ የበለጠ ቅርብ ነው፡፡ ከክፍለ ሀገር አካባቢ ሰዎች ደውለውልኝ ያውቃሉ፡፡ ´ሬዲዮ ላይ ስምህን ሰማሁ ለካ ትራፊክ ሆነሀል´ ያለኝ ሰው አለ፡፡ ሌላም የፖሊስ መረጃ ፍለጋ የደወሉ አሉ፡፡ አይ እኔኮ አትሌቱ ነኝ እያልኩ እመልሳለሁ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ከኢንስፔክተሩ ጋር በቅርበት ትተዋወቃላችሁ?

አሠፋ፡- አዎ! ቀደም ሲል እንዲያውም እርሱ ራሱ ሲያገኘኝ ´ያንተ ስም ለእኔ አልጠቀመኝም፡፡ ከሀገር ቤት እየደወሉ ´አንተ በቃ ሯጭ ሆንክ? እያሉ መከራዬን እያበሉኝ ነው´ እያለ ያስቀኝ ነበር፡፡ አሁን ተራዬን አንተ ትራፊክ ሆነሃል እየተባልኩ ነው፡፡ አዳዲስ ሰዎች ስተዋወቅ አሠፋ መዝገቡ እባላለሁ እል ነበር፡፡ ታዲያ አንዳንዶቹ ´አሀሀ…ጠዋት ጠዋት ሰው ሞተ የምተለው አንተ ነሃ´ እያሉኝ ተቸገርኩ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አትሌት የሚለውን ጨምሬበት ´አትሌት አሠፋ መዝገቡ´ እላለሁ፡፡… (ይስቃል)

ዱብ ዱብ፡- ከታላቁ ሩጫ ጋር በበጎ ፈቃደኝነት ትሰራለህ፡፡ ትውውቃችሁ መቼ እና እንዴት እንደነበር አስታውሰን፡፡

አሠፋ፡- የዛሬ 17 አመት የታላቁ ሩጫ ሀሳቡ ሲጀመር ቅርብ ነበርኩ፡፡ የመጀመሪያውን ውድድርም ተሳትፌያለሁ፡፡ ሀይሌ ሲያሸንፍ እኔ ሁለተኛ ነበርኩ፡፡ ከሁለተኛው አንስቶ ለትምህርት ከሀገር ውጪ ከቆየሁባቸው አመታት በስተቀር በስራ አብሬያቸው ነበርኩ፡፡

ዱብ ዱብ፡- በእነዚህ አመታት ከታላቁ ሩጫ የትኛው ለውጡ ይበልጥ አስደነቀህ? 

አሠፋ፡- የመጀመሪያው ሩጫ ላይ በአትሌትነት ከተሳተፍኩ በኋላ የተሳታፊው ህዝብ ስርዓት አስገርሞኛል፡፡ በአንደኛው ውድድር መነሻ እና መድረሻ ላይ የነበረው መተረማመስ እና የአሁኑ ልዩነት ይገርማል፡፡ ለዚያውም የተሳታፊው ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሮ የተሳታፊው ስርዓት ልዩ ነው፡፡   

ዱብ ዱብ፡- የአትሌትነትህን ዘመን ስታስብ ምን ይቆጭሀል?

አሠፋ፡- ብዙ የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ እግዚአብሔር የወሰነልኝን ሁሉ አግኝቻለሁ፡፡ ሩጫ ኑሮዬ እንደሚሆን አላውቅም ነበር፡፡ ከተወለድኩበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት ለትምህርት ነው፡፡ ተፈሪ መኮንን እየተማርኩ ነው መሮጥ የጀመርኩት፡፡ በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በአትላንታ ኦሊምፒክ ወጣት ነበርኩ፡፡ 2ኛውን ማጣሪያ ሳላልፍ ቀረሁ፡፡ ከአራት አመት በኋላ ሜዳሊያ ለማግኘት አቅጄ በሲድኒ ተሳካልኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ ከአራት አመት በኋላ ወርቅ ለማግኘት አለምኩ፡፡ ለዚያ ህልሜ ስሰራ ነው በጉዳት ሩጫ ያቆምኩት፡፡

ዱብ ዱብ፡- ስለ ቁጭት ካነሳን… ብዙ ሰዎች ስለ አንተ የሚቆጩበትን የኤድመንተን የአለም ሻምፒዮና ላስታውስህ፡፡ ቻርለስ ካማቲን ለማሸነፍ እድሉ እንደነበረህ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ተመሳሳይ ስሜት አለህ? 

አሠፋ፡- አዎ እድሉ ነበረኝ፡፡ ከካማቲ ጋርም ሌሎች በርካታ ውድድሮች ላይ እንተዋወቃለን፡፡ ሆኖም ለቡድን እቅዳችን ተገዢ ነበርን፡፡ ካማቲ ሲወጣ ማመን ስላልቻለኩ ዞሬ ሀይሌን ፈለግሁት፡፡ ሆኖም በመቶ ሜትር ውስጥ ነገሮችን ለመለወጥ ረፍዶብን ነበር፡፡ ሀይሌ ከሲድኒ መልስ እግሩ ህመም ነበረው፡፡ ስለዚህ ከውድድሩ በፊት ተነጋገርን፡፡ ህመሙ ከተሰማው ለእኛ የራሳቹን ሩጫ ሩጡ ብሎ ምልክት ሊሰጠን ተስማምተን ነበር፡፡ ሩጫው ሲያልቅ ከሀይሌ ጋር አወራን፡፡ ደህና ነበርኩ አለኝ፡፡ እሱ ራሱ (ካማቲ) ከህዝብ መሀል የወጣ ነው የመሰለኝ እንዳለኝ ትዝ ይለኛል፡፡ (ረጅም ሳቅ)

ዱብ ዱብ፡- እናመሰግናለን አሴ! አሠፋ፡- እሺ እኔም አመሰግናለሁ!         

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ