አምለሰት – ስለ ሩጫ፣ ስፖርት እና የኑሮ ዘይቤ

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

እንግዳችን አምለሰት ሙጬ ነች፡፡ ሞዴል፣ ተዋናይት፣ የፊልም ጸሀፊ፣ እና ሌሎች ብዙ የምትታወቅባቸው መገለጫዎች አሏት፡፡ በዱብ ዱብ መጽሔታችን ግን ምናልባት ብዙዎች ስለማያውቁት ሯጭነቷ እንጫወታለን፡፡  

ዱብ ዱብ፡- በውድድሮች ላይ የመሳተፍ ልማድ አለሽ ማለት ነው?

አምለሰት፡- አዎ. . . ለcause እሮጣለሁ፡፡ በታላቁ ሩጫ እና በሀዋሳ የሴቭ ዘ ችልድረን ሩጫ እና የመሳሰሉት ላይ ስሮጥ ነበር፡፡

ዱብ ዱብ፡- በሴቶቹ ሩጫ 5ኪ.ሜ. ያሸነፍሽበት ምርጡ ሰዓትሽ ነው?

አምለሰት፡- እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሰዓቴን አልመዘገብኩም፡፡ ትሪድሚል/የሩጫ ማሽን/ ላይ ግን 5ኪ.ሜ ከዚያም ባነሰ ሰዓት እጨርሳለሁ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ከወሊድ በፊትና በኋላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መቀጠል እና መልካም አቋም መመለስ ከባድ አይደለም?  

አምለሰት፡- ከወሊድ በፊት ጥቂት ጊዜ እስኪቀረኝ ድረስ ስፖርት አላቆምኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ስፖርት የኑሮ ዘይቤዬ ነው፡፡ ከድሮም ስፖርት እሰራለሁ

ዱብ ዱብ፡- ብዙ ጊዜ የአካል ብቃት እንቅስቃሴሽን የምትሰሪው ቤት ውስጥ? በጎዳና ላይ ሩጫ? ጂም ውስጥ?

አምለሰት፡- ከቤት ውጪ ሩጫ እንኳን እሰራ የነበረው ጥቂት ቆየት ብሏል፡፡ አንድ-ሁለት አመት ይሆነኛል፡፡ በዚያ ጊዜ አንድ ሙቪ እየሰራሁ ነበር፡፡ ትልቅ ሙቪ ነው፡፡ ገና አልወጣም፡፡ ፕሮዳክሽኑ ከውጪ መጥቶ ነው የሰራነው፡፡ ታሪኩን የጻፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ገጸ ባህርይዋ አንዲት ሯጭ የመርካቶ ልጅ ናት፡፡ እኔ ሩጫን እንደ symbol ነው የማየው፡፡ እዛ (ፊልሙ) ላይም ሩጫን እንደ ካራክተር ነው የተጠቀምንበት፡፡ ሰው በተሰማራበት ማንኛውም መስክ ቢሮጥ እንደማለት ነው፡፡ አትሌቶቻችን ስማችንን ቀይረውልናል፡፡ ቀደም ብሎ በድህነትና ረሀብ ብቻ የሚያስታውሱን ሰዎች አሁን ኢትዮጵያ ሲባል “ኦ… የጎበዝ ሯጮች ሀገር” እስከመባል ደርሰናል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በፊልሙ ላይ ካራክተሯ ይህንን ሀሳብ ይዛ ነው የምትሮጠው፡፡ ሁሉም ሰው በተሰማራበት ነገር ቢሮጥ የኢትዮጵያ ገጽታ ይቀየራል፡፡ ህዝባችንም ህይወቱን መቀየር ይችላል የሚለውን ሀሳብ ለማስተላለፍ የመጣልኝ ሀሳብ ነው፡፡ ይሄ ሀሳብ እየሰፋ ሄዶ ፊልም ደረጃ ደርሶ አሁን አልቋል፡፡ በዚህ አመት ይወጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ዱብ ዱብ፡- ለመጨረሻ ጊዜ ያየሽው የአትሌቶቻችን ውድድር?

አምለሰት፡- በቅርብ ገንዘቤ ያሸነፈችበትን ውድድር (የበርሚንግሀም የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና)

ዱብ ዱብ፡- ከወሊድ በፊት/በኋላ የምትሰሪያቸው የስፖርት እንቅስቃሴዎች ምን አይነት ነበሩ?

አምለሰት፡- በእርግዝና ጊዜዬ ቀለል ያሉ ለእኔም ለልጄም ተስማሚ የሆኑትን እሰራለሁ፡፡ ለምሳሌ ቀለል ያለ እርምጃ ትሪድ ሚል ላይም ቢሆን፡፡ እንደ ዮጋ ቀለል ያለ፡፡ ዋናም እንደዚሁ ቀለል ያለ አድርጌ እሰራለሁ፡፡ ራሴ ላይ ብዙ ጫና አልፈጥርም፡፡ ከወሊድ በኋላ ግን አንድ አመት አርፌ ነው የምጀምረው፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ ለአንድ አመት ጡት ማጥባት አለብኝ፡፡ በደንብ ታርሼ እና ወፍሬ ነው የወጣሁት /ሳቅ/፡፡

ዱብ ዱብ፡- ከሰውነት ክብደት መጨመር በኋላ ወደ ቀደመው መመለስ ምን ያህል ከባድ ነው?

አምለሰት፡- እውነት ለመናገር በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔም ስፖርት ስለመሰራ በቀላሉ እደምመልሰው አስቤ እናቴና አማቼ የሰጡኝን ሁሉ በልቼ በጣም ወፍሬ ነበር፡፡ ወደ 30 ኪሎ ጨምሬ ነበር፡፡ 80 ኪሎ ደርሼ ነበር፡፡ አሁን ወደ 60 ወርጃለሁ፡፡ ፊልሙ ላይ ደግሞ 56 ኪሎ ነበርኩኝ፡፡ ስፖርቱን ሳላቋርጥ እሰራ ነበር፡፡

ዱብ ዱብ፡- በአመጋገብ በኩል የተለየ የባለሙያ ምክር ተጠቅመሽ ነው ወይስ…?

አምለሰት፡- እምም… አነባለሁኝ፡፡ Diet የሚባለውን ነገር ብዙ አላምንበትም፡፡ ሞክሬው አውቃለሁ. . . ግን ከጤናም አኳያ ብዙ የተስማማኝ ነገር አይደለም፡፡ አሁን ያመንኩበት ነገር ትክክለኛ የኑሮ ዘይቤን ልማድ ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ በአመጋገብም እንደዚያው፡፡ ቅባት አለማብዛት፡፡ በአንድ ጊዜ ብዙ አለመብላት፡፡ ራት ላይ ቀለል ያለ ነገር መብላት፡፡ እነዚህን ነገሮች አሁን እንደ ስፖርቱ ሁሉ የኑሮ ዘይቤዬ እያደረግኳቸው ነው፡፡ ከወሊድ በኋላ ሰውነትን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ የፈለግከውን እየበላህ ሰውነት የቀደመውን መሆን አይችልም፡፡

ዱብ ዱብ፡- ክብደት መቀነስ የብዙ ሰው ፍላጎት ነው፡፡ ሆኖም የሚሳካለቸው ብዙዎች አይደሉም፡፡ እንዳይሳካላቸው የሚሳሳቱት የሚመስልሽ ነገር ምንደንው?

አምለሰት፡- መጀመሪያ የእውነት ያንን ነገር ከጠላኸው ማድረግ እችላለሁ ብለህ ማመን ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንም ሳይመስለን የኖርንበት ነገር ይሆንና ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን ቀድሞ ያልነበረ እና አሁንም ያልፈለግከው ነገር ከሆነ ልትለውጠው ትችላለህ ብዬ አምናለሁ፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የህይወትህ አንድ ክፍል ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ለእኔ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለስፖርት መኖር የምችል አይመስለኝም፡፡

ዱብ ዱብ፡- እንግዲህ በብዙ የጥበባዊ ስራዎች ላይ በተለያየ ሚና ትሳተፊያለሽ፡፡ የስፖርታዊ እንቅስቃሴሽን አብልጦ የሚጠይቀው የትኛው ሚናሽ /ስራሽ/ ይመስልሻል?

አምለሰት፡- እኔ በመጀመሪያ ራሴ  ስለምፈልገው ነው፡፡ ለስራዬ ብቻ ብዬ አይደለም፡፡ እንደዛ ከሆነ ስራው ሲቆም ስፖርቱም ሊቆም ነው፡፡   

ዱብ ዱብ፡-  ስፖርትን ባጠቃላይ ሳታቋራጪ ስንት አመት ሰራሽ

አምለሰት፡- ቴክዋንዶ ከመማር ጀምሮ ከዚያ ዋና ውስጥ መግባት ከዚያም ሳልሳ ዳንስ በኋላም ፈረስ መጋለብ… የኑሮ ዘይቤዬ በጣም በእንቅስቃሴ የተሞላ ነው፡፡ ቁጭ በማለት ወይም በአንድ ነገር መያዝ አልችልም፡፡ ህይወቴ ሁሉጊዜም የእንቅስቃሴ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ እያደገ የመጣውም ያ ይመስለኛል፡፡

ዱብ ዱብ፡- በሴቶቹ ሩጫ የተምሳሌቶቹን ምድብ አሸንፈሽ ስትገቢ ርቀቱን የጨረሽበት ሰዓት አስደናቂ ቢሆንም የተጋነነ ድካም አልታየብሽም፡፡

አምለሰት፡- አዎ ራሴን ብዙ ተጭኜ አልሮጥኩም፡፡ በተመሳሳይ ፍጥነት ነበር የምሮጠው፡፡ ከ30 ደቂቃ በታች እንደምገባ እርግጠኛ ነበርኩኝ፡፡ ነገር ግን 25 ደቂቃ አልጠበቅኩም፡፡ ራሴን ሳላጨናንቅ 27 አካባቢ መሮጥ ነበር ሀሳቤ፡፡ ሰርቲፊኬት የሚያገኘው በ35 ደቂቃ የገባ ነው ስለተባለ. . . ያው ገንዘብ ስለሌለው (ሳቅ). . .ቢኖረው ደሞ ማሰብ ነው. . .(ሳቅ)፡፡ ሀሳቡ ትልቅ ነው፡፡ ካለው cause ጋር ሴቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ ግንዛቤ ለመፍጠር አብሮ መስራት ደስ ይላል፡፡

ዱብ ዱብ፡- መንገድ ላይ ምን ገጠመሽ? ከፍቅር አድናቆት የመጣ ሩጫሽ አልተስተጓጎለም?

አምለሰት፡- ብዙ ሞራል ተሰጥቶኛል፡፡ በርቺ ሲሉኝ ፍጥነቴን ጨመር አደርግና ወደ ኖርማል እመለሳለሁ፡፡ አምለሰትማ አትቀድመነንም ብለውም ከኋላዬ ይሞክሩኝና ትንሽ አብረውኝ ከሮጡ በኋላ ይቀሩ ነበር፡፡ እኔ በራሴ ፍጥነት ነበር የምሄደው፡፡                                            

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ