ታላቁ ሩጫ ላይ ያላሸነፍኩባቸው አምስት ሰበቦች (ሎል

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

ታላቁ ሩጫ እንደ እንቁጣጣሽ የሕዝብ በዓል መሆኑ ሁሌም ሲደርስ ብቻ ነው የሚገባኝ፡፡ የዘንድሮው ትኬት በአንድ ሳምንት ተሸጦ በማለቁ፣ ከአትራፊዎች ለመግዛት ያላየነው ፍዳ አልነበረም – ደግነቱ ተሳክቷል፡፡ ነገር ግን ‹‹እንደተጠበቅኩት›› አንደኛ ሳልወጣ ቀርቼያለሁ፡፡ ሰበብ አለኝ፡፡ ምናልባት እናንተ ግምታችሁን ስትሰነዝሩ ‹‹ጫማው ስለጠበበው፣ በዋዜማው የበላው እራት ስላልተስማማው፣ ውድድሩ በተጀመረ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ሆድ ቁርጠት ስለጀመረው፣ የዳኞች አድሎ ስለነበር….›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ግን በተሳሳተ ግምት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚወናበድ በሚል እውነተኛዎቹን ምክንያቶች እንደሚከተለው ለመዘርዘር ወስኛለሁ፡፡
በነገራችን ላይ አንደኛ ባለመውጣቴ የደረሰብኝን መሪር ሐዘን በስልክ፣ በደብዳቤ፣ በጋዜጣዊ መግለጫ፣ በፌስቡክ አስተያየት እና በአካል በመገኘት ላፅናናችሁኝ እና ለምታፅናኑኝ ሁሉ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡

1ኛ – የቆነጃጅቱ ተሳትፎ
በታላቁ ሩጫ የተለያየ (መልክ፣ ቁመና፣ አሯሯጥ፣ አሳሳቅ እና ወዘተ ላይ የተመሰረተ) ቁንጅና ያላቸው ሴቶች ተሳትፈው ነበር፡፡ የነርሱ መሳተፍ በኔ አንደኛ አለማውጣት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ምን እንደሆነ ግራ ከገባችሁ የዋሆች ናችሁ ማለት፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ቆነጃጅት ጥሎ መሮጥ በጣም እንደሚከብድ ወደፊት በጥናት የሚረጋገጥ ቢሆንም ላሁኑ ግን ያየው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ ከነርሱ ኋላ፣ ኋላ እየተከታተልኩ ስሮጥ ለካስ ቀድሞኝ የገባ ተወዳዳሪ ነበር – አላየሁትም፡፡ ይህንኛው ዋንኛው ምክንያት ቢሆንም ሌሎችም አሳማኝ ሊባሉ የሚችሉ አሉ፡፡


2ኛ – ማቋረጥ አለመቻሌ
በርካታ ተፎካካሪዎቼ የአገር አቋራጭ ሩጫ የሚለውን በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱት የገባኝ አቋራጭ ሲፈልጉ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ግማሽ ላይ ጀምረዋል፣ ሌሎቹ መጀመሪያ እና መጨረሻው ላይ ብቻ ተገኝተው መሃሉን ሲያሳብሩ ታይተዋል፡፡ እኔም ይሄንኑ ማድረግ ፈልጌ የነበረ ቢሆንም አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱም ስሙን ጀርባዬ ላይ የፃፈው ኩባንያ መልካም ገፅታዬን አጎደፍክ ብሎ ፍርድ ቤት ይገትረኛል ብዬ ፈራሁ፡፡
3ኛ – ከፊት፣ ከፊት ጭፈራ የለም
የቀደሙኝ ሰዎች እነዚህ ብቻ ናቸው::የሌላውን ተወዳዳሪ አላውቅም፤ እኔ ግን ሕዝባዊ ጭፈራ ላይ የምሳተፈው በዓመት አንዴ በታላቁ ሩጫ ላይ ነው፡፡ ታዲያ በታላቁ ሩጫ ላይ የደራ ጫወታ እና ጭፈራ ያለው ወደኋላ እንጂ ወደፊት ባለመሆኑ አውቄ (ጭፈራ ፍለጋ) ወደኋላ ማፈግፈጌን አልሸሽጋችሁም፡፡ እንዲያም ሆኖ ከፊቴ የነበረችው ቆንጆ በጣም ትሮጥ ነበር ማለት ነው እሷን ስከተል ያመለጠኝ ጭፈራ እንዳለ ከኋላ የቀሩት ጓደኞቼ ነግረውኛል፡፡ እኔ የነበርኩበት ቡድን ለዛ ያለው ጭፈራ ትቶ መሽቀዳደምን ወግ አድርጎት ነበር፡፡ እኛ የጨፈርነው ‹‹ኃይሌ ቢያቆምም፣ እኛ አናቆምም›› እያልን ነው፡፡ እውነታችንን ነበር፡፡ ዞሮ፣ ዞሮ ግን ጭፈራችንም፣ ግብራችንም ሩጫ ነበር፡፡ ይኸው ኃይሌ ታላቁ ሩጫ ላይ መወዳደር ካቆመ ድፍን ዘጠኝ ዓመቱ – ታዲያ መቼ እኛ አቆምን?

ከዚህ በተጨማሪም በመንገድ ላይ በምናገኛቸው የጃዝ ባንዶች አልፎ፣ አልፎ ዳንኪራ የወረድኩ ሲሆን አንዳንድ የስፖርት ተንታኞች እንደገለፁት ከሆነ ለዳንኪራ ያባከንኩት ጉልበት በአጨራረስ እንድበለጥ አድርጎኛል፡፡

4ኛ – ትኩረት ማጣት
እኔ በታላቁ ሩጫ ለመሳተፍ ስወስን ዳር ላይ የሚደረደረው ሕዝብ ይመለከተኛል ብዬ ገምቼ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ በየመንገዱ ዳር የተኮለኮሉት ተመልካቾች ትኩረት አጀብ ብለው በሚሮጡት ሰዎች ላይ በመሆኑ ከአጀቡ ተለይቼ ለመውጣትም ሆነ ለመታየት አልቻልኩም፡፡ እንግዲህ አኔም አጀብ ፍለጋ ስንከራተት አንዳንድ የ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ባሕሪ የተጠናወታቸው ተወዳዳሪዎች ጥለውኝ ተፈተለኩ፡፡ እነዚህን ሁሉ ቀድሜ ነበር::

5ኛ – ወጪው እያደናቀፈኝ
ታላቁ ሩጫን ለመሮጥ የቲሸርት መግዣ ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው፡፡ መሮጫ ትጥቅ ያስፈልጋል፡፡ እሱን ተዉት እኔን የጎዳኝ ትንፋሼን ለማዳበር እና ጡንቻዬን ከመሸማቀቅ ለመታደግ ብዬ ሁለት ሳምንት አስቀድሜ ቀላል ልምምድ ሳደርግ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ የዕለት የምግብ ወጪዬ በእጥፍ አሻቅቧል፡፡ በዚህም የወር ገቢዬ ወር ሳያደርሰኝ አልቋል፡፡ ይህንን እያሰቡ መሮጥ ለአንድ አትሌት ፈታኝ እንደሆነው፣ ሁሉ ለእኔም ሲያደናቅፈኝ ነበር፡፡
እነዚህን ምክንያቶች ከግምት ውስጥ ያስገቡት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በመጨረሻ ሜዳሊያ ስላጠለቁልኝ ስሮጥ በደገፉኝ፣ ስወድቅ ባነሱኝ እና ስሸነፍ ባፅናኑኝ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ስም አመሰግናቸዋለሁ፡፡

(በፈቃዱ ዘ. ሀይሉ)፤ 2003

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ