“ታላቁ ሩጫ – ለተስፈኞች ተስፋ” ይግረም ደመላሽ

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

ይግረም ደመላሽ – የሪዮ ኦሊምፒክ ዲፕሎማ ተሸላሚና የመጪው ዓለም ሻምፒዮና ተስፈኛ

ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ጎጃም ደጋ ዳሞት ወረዳ ልዩ ስሙ ድኩል ቃና በሚባል ስፍራ ሲሆን በግብርና ስራ የሚተዳደሩት ወላጆቹ ካፈሯቸው ሁለት ወንድ እና ሁለት ሴት ልጆች ሶስተኛው ነው፡፡ በልጅነቱ በእረኝነት ስራ ቤተሰቦቹን ከማገዙ ጎን ለጎን የገና ጨዋታን ጨምሮ ሩጫ የተቀላቀለባቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያዘወትር ነበር፡፡ የሩጫ ውድድር ላይ መሳተፍ የጀመረው በ1997 ዓ.ም. በትውልድ ስፍራው የሰባተኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት የ8 ኪሎ ሜትር የትምህርት ቤቶች አገር አቋራጭ ውድድር ላይም አምስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ይህ አትሌት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 11ኛ ውድድር የብር ሜዳልያ ባለቤት ይግረም ደመላሽ ነው፡፡

በትውልድ ሀገሩ ፈረስ ቤት በሚባል ፕሮጀክት ውስጥ አብራው የነበረችው እመቤት አንተነህ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ስኬታማ መሆን መቻሏ እንዲሁም በመገናኛ ብዙሀን የተከታተላቸው የሀይሌ ገ/ስላሴ እና ኢብራሂም ጄይላን የ10 ሺህ ሜትር ድሎች ይግረም በሩጫው ስኬታማ ለመሆን ይበልጥ እንዲታትር ካነሳሱት ምክንያቶች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በፈረስ ቤት ሀይ ስኩል ቆይታው በጓደኛው ጋባዥነት የሩጫ ልምምድን በትኩረት ወደ መስራት የተሸጋገረው ተስፈኛ ወጣት በዛው የክልሉን የፕሮጀክት ሰልጣኞች ስብስብ ተቀላቅሎ ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. በፕሮጀክት ሰልጣኝነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በፕሮጀክት ቆይታው የመጨረሻ ዓመት (በ2003 ዓ.ም መጨረሻ) ላይ በአዲስ አበባ በተካሄደ የፕሮጀክቶች ውድድር ክልሉን ወክሎ በመሳተፍ በ5000ሜ. ከሀጎስ ገ/ሕይወት ቀጥሎ ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ በ10,000ሜ. አንደኛ በመውጣት አሸንፏል፡፡ በዛ ውድድር ላይ ያሳየው ድንቅ ብቃት መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች የአትሌቲክስ ክለብን ለመቀላቀል ያስቻለው ሲሆን ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድንም ለመመረጥ አብቅቶታል፡፡

ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ በ2004 ዓ.ም. በተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል 10 ኪ.ሜ. ውድድር ላይ ተሳትፎ ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው ይግረም ‹‹ሽልማቴን የተቀበልኩት ከታላቁ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ እጅ ነበር፡፡ በጣም የማደንቀው እና መቼም በአካል አገኘዋለሁ ብዬ የማላስበው ሀይሌ ሊሸልመኝ ሲመጣና ሲጨብጠኝ በአድናቆት ፍዝዝ ብዬ ስመለከተው ነበር›› በማለት ያስታውሳል፡፡  በወቅቱ በታላቁ ሩጫ ላይ ያስመዘገበው ውጤት ማናጀር ለማግኘት እና በዓለም አቀፍ የግል ውድድሮች ላይ ተሳታፊ መሆን የቻለበትን የዕድል በር በሰፊው እንደከፈተለት ይናገራል፡፡ ‹‹እኔን ለመሳሰሉ ጀማሪ አትሌቶች የመታያ ዕድል የሚሰጠውን ይህን ውድድር ለሚያካሂዱት አካላት ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡››       

በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በስፔን ባርሴሎና በተካሄደው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ. የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና የ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክም አራተኛ በመውጣት የዲፕሎማ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡        

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ