ሚያዚያ 7 ቀን 2014፡- አገራችን ከምትታወቅባቸው መልካም ዕድሎች መካከል አትሌቲክስን መሠረት ያደረገው የስፖርት ቱሪዝም አንዱ ነው፡፡ ይህን መልካም ዕድል ወደ ተሟላ አገር አቀፍ ስኬታማነት ለመቀየር እንዲረዳ ቦቆጂን ማዕከል ያደረገ አገር አቀፍ ፕሮግራም ለማካሔድ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው፡፡
ኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን የምትገኘው ቦቆጂ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ከፍ ብላ እንድትጠራ ያስደረጉ ስመ ጥር ዓለም አቀፍ አትሌቶች ፡- ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን፣ ቀነኒሳ በቀለን እና ጥሩነሽ ዲባባን ያፈራች ከተማ መሆኗ፤ አትሌትክስን ለማበረታታት እና ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡
የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‘’ኢትዮጵያ ትሮጣለች’’ በሚል መሪ ቃል በቦቆጂ ከተማ ግንቦት 6 እና 7 ቀን 2014 ዓ.ም የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ያካሂዳል፡፡
የዝግጅቱ ዋና ዓላማ የስፖርት ቱሪዝምን፣ በተለይም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት፣ የእውቅ ዓለም አቀፍ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችውን ቦቆጂ ከተማን ለማስተዋወቅ እና ከተማዋ እንድትነቃቃ በማድረግ ለአዳጊ አትሌቶች ጥሩ የመወዳደሪያ መድረክ ለመፍጠር ነው፡፡
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የ2014 ታላቁ ሩጫ ቦቆጂ፣ በአርሲ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የተራራ መውጣት፣ የብስክሌት ውድድር እና በስመ ጥሩዋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣‘’ጥሩነሽ ዲባባ ሻሚፒዎንሽፕ’’ በመባል የተሰየመው ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በሆኑ አዳጊ አትሌቶች መኻከል ውድድር ይደረጋል፡፡ ታዋቂ አትሌቶች፣የቦቆጂ እና አካባቢው ኗሪዎች እና ከአዲስ አበባ የሚጓዙ ጤናቸው ለመጠበቅ የሚሳተፉ ሯጮቾን ጨምሮ 1200 ሰዎች ይሣተፋሉ፡፡
ቱሪዝም ሚንስቴር ቦቆጂና አካባቢውን የሚገልፅና የቱሪስት መስህብ የሚሆን መለያ ምልክት (land mark) ያስቀምጣል፡፡
በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የረጅም ርቀት አሸናፊዎችን በማፍራት የሚታወቀው የኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ ከቦቆጂ ከተማ ጋር የከተሞች እኅትማማችነትን ለመመሥረት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡ ፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ታዋቂ ከሆኑት ውድድሮች አንዱ የሆነው ኤልዶሬት ሲቲ ማራቶን፤ የ2014 ታላቁ ቦቆጂ ሩጫ ላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በሚቀጥለው ዙር በኤልዶሬት ከተማ ተገኝተው የውድድሩ ተጋባዥ ተወዳዳሪዎች እንዲሆኑ ተስማምቷል፡፡
ይህ ዕድል በተለይ አዳጊ አትሌቶች የተሻለ ተመክሮ እንዲቀስሙ ከመርዳቱ በላይ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የመወዳደር ልምድ እንዲያካብቱ የሚረዳ ሲኾን የኹለቱን ከተሞች እኅትማማችነትን በማጠናከር የቱሪዝም ፍሰትን እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡
ለበለጠ መረጃ፡- ሕሊና ንጉሴ 0911601710 ወይም hilina@ethiopianrun.org