ስፖርት እና ማህበረሰብ

Share This Post

Share on facebook
Share on linkedin
Share on twitter
Share on email

ቀለል ያለው አለባበሱ በስፖርት የዳበረ ሰውነቱን ባይደብቅበትም ስፖርተኞቹን መቀላቀል አልፈለገም፡፡ የ39 ዓመቱ ውብሸት መንግስቱ ጥግ ይዞ አድፍጧል፡፡  የሀዋሳ ግማሽ ማራቶን በተካሄደበት ባለፈው የሚያዚያ አጋማሽ እሁድ ጠዋት አስቀድመው “ገብርኤል አደባባይ” አቅራቢያ የተሰባሰቡትን ሯጮች በተመስጦ ይመለከታል፡፡

“ታውቃለህ… ከሯጮቹ የማውቀው ሰው አላየሁም” ይላል በመገረም የአንድ እጁን መዳፍ አፉ ላይ ጭኖ፡፡ የእድሜውን ሶስት አራተኛ በሀዋሳ የኖረው ውብሸት እንደ ቀደመው ጊዜ በከተማዋ የሚኖሩ ብዙ ሯጮች፤ ዋናተኞች፤ ብስክሌተኞች እና ሌሎችም ስፖርተኞችን አለማየቱ ይቆጨዋል፡፡  

“ሀዋሳ ተለውጣለች፡፡ ከልክ በላይ ውፍረት ችግራችን አልነበረም፡፡ አሁን ወጣቶቹ ገና በ20ዎቹ እድሜ ክብደታቸውን መቆጣጠር ሲቸገሩ ታያለህ፡፡ ግማሽ ማራቶን መሮጥን ተወው፡፡ 10 እና 5 ኪሎ ሜትር… ኧረ እሱንም ተወው፡፡ የአሁኑ ወጣት እርምጃውስ መቼ ሆነለት?” ብሎ ይስቃል፡፡ “የሀዋሳ ነዋሪ ከሆንክ ሞተር ብስክሌት ይኖርሀል፡፡ ከሌለህም ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ወይም ታክሲ ትሳፈራለህ፡፡ ለመራመድ የአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት እንኳን አትታገስም፡፡ ታዲያ… ላትወፍር ነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡

የ27 ዓመቷ ዘሪቱ ጎአ በአደባባዩ የተገኘችው ልጇን ይዛ ነው፡፡ ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ልጇ የሰውነት ክብደት ያሳስባታል፡፡ “ሩጫ ክብደት ለመቀነስ የተሻለው ስፖርት መሆኑን እሰማለሁ፡፡ ግን ልጄን እንድትሮጥ ለማድረግ ብዙ እድል አላገኘሁም፡፡ የዛሬው አይነቱ ልጆች በቁጥር ብዙ ሆነው የሚሮጡበት እድል ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በውድድሩ እሷ ስትሮጥ ከጎኗ ልከተላት ሞክሬ ነበር፡፡ ስንት ሜትር እንደተከተልኳት አላውቅም እንጃ፤ ወዲያው እኔ ራሴ ማለክለክ ጀመርኩ” ብላ ትስቃለች፡፡

“በእርግጥ በሀዋሳ የእግር እርምጃ (ዎክ) ማድረግ የሁሉም ሰው ልማድ ነበር” ትላለች ዘሪቱ፡፡ “በቀደመው ጊዜ ከ11 ሰዓት በኋላ ነዋሪው ብቻ ሳይሆን የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችም በቁጥር በርከት ብለው በተመሳሳይ አቅጣጫ ሲሄዱ ይታዩ ነበር፡፡ ካፌ ራታቸውን በጊዜ በልተው እየተጫወቱ ወደ ሀይቁ ይመጣሉ፡፡ ጸሀይዋ ስትጠልቅ በአይናቸው ሸኝተዋት እንደ አመጣጣቸው በእግራቸው ይመለሳሉ፡፡ አሁን እንቅስቃሴያቸው ሁሉ በሞተር ብስክሌት እና በባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ ነው፡፡”

በ1995 ለትምህርት ሀዋሳን የረገጠው ዘመላክ እንድሪያስ ቢያንስ ባለፉት 13 ዓመታት የተመለከተውን ለውጥ ይናገራል፡፡ “ከ10 ዓመት በፊት ሀዋሳ ውስጥ ቦርጫም ሰዎችን በብዛት ስለማየቴ እጠራጠራለሁ፡፡ ምናልባት ጥቂት በእድሜ የገፉ ሰዎች ካልሆኑ በስተቀር፡፡ አሁን ከ20ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ስብ ያከማቹ ሰዎች ታያለህ፡፡ ይሄ የሌሎችም ከተሞችና የተቀረው አለም ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ውፍረት እንደ Normal መታየቱ ነው፡፡ ወጣቱ ትርፍ ስጋ መሸከሙ በግልጽ እየታየም ቦዲ (ጠበብ ያሉ ልብሶች) ሲመርጥ ትታዘባለህ፡፡ ከሰውነት ቅርጽ ይልቅ ሰው በልብሱ ብራንድ መደነቅ የመረጠ ይመስለኛል፡፡”

በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ይታወቁ የነበሩ ሜዳዎች አሁን በቁጥር መንምነዋል፡፡ በብሄራዊ ቡድን የምናውቃቸውን አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለ እና ሙሉጌታ ምህረት የመሳሰሉ ተጫዋቾች ልጅነታቸውን ካሳለፉባቸው ሜዳዎች ውስጥ አሁን ያሉት በቁጥር ብዙ አይደሉም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእድሜ ከፍ ያሉትና ለጤናቸው ስፖርት የሚያዘወትሩ በርካቶች በወልደአማኑኤል ዱባለ ተብሎ በሚታወቀው አደባባይ አካባቢ አስፋልት ላይ ሲንቀሳቀሱ መታየት መጀመራቸው መልካም ነው፡፡ ወጣቱ ግን በተቃራኒው በሱስ ወደ መጠመድ ማዘምበሉን ነዋሪዎች ይታዘባሉ፡፡

“እንዲህ ያለው ውድድር (የሀዋሳ ግማሽ ማራቶን) ወጣቱ ራሱን እንዲያይ እድል ይሰጣል፡፡ ለረጅም ጊዜ ስፖርት ስታቆም ለውጥህን ተቀምጠህ አታስተውለውም፡፡ ለውድድር ስትዘጋጅ ወይም ጥቂት ኪሎሜትሮች ልትሮጥ ስትሞክር ደረጃህን ታውቃለህ፡፡ ምናልባትም በቋሚነት ጂምናዚየም ለመስራት ወይም በግል ለመንቀሳቀስ ማቀድ ትችላለህ” ይላል ውብሸት፡፡

ዘመላክ ድንበር ተሻግሮ ለስራ በተጓዘበት ጎረቤት ሀገር የገጠመውን አይረሳም፡፡ ናይሮቢ ውስጥ ሀሩራ ፎረስት የተሰኘ ቦታ እየጎበኘ በስራ አጋጣሚ ከተግባባት አንዲት ስዊድናዊት ጋር ጨዋታ ይይዛል፡፡ ብስክሌተኛ እንደሆነች ስትነግረው እርሱም ከሀዋሳ መምጣቱን እና የደቡቧ ከተማ እንደ ባህርዳር ሁሉ በጎበዝ ብስክሌት ጋላቢዎች የተሞላች ስለመሆኗ ይነግራታል፡፡ እርሷም በአጋጣሚው ተደስታ “የሚገርምህ እዚህ ብስክሌት የመጋለብ እቅድ ነበረኝ፡፡ ፓርኩን በብስክሌት እንድንዞር ፈቃደኛ ነህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡ “እንዴታ!” 12 ኪሎ ሜትሩን ርቀት ጀመሩት፡፡ የእርሷን ፍጥነት ሊስተካከል በሞከረ መጠን አቅም አነሰው፡፡ “ከሶስት ኪሎሜትሮች በኋላ ወርጄ ብስክሌቴን መግፋት ነበረብኝ” ይላል ራሱን በትዝብት እየነቀነቀ፡፡ ዘመላክን የመሰሉ ጥቂቶች ከተሜነት የሀዋሳን ነዋሪ ከመታወቂያው (ስፖርት) እየነጠለው መሆኑን የማስተዋል እድል አግኝተዋል፡፡ ዘሪቱ ልጇን ሩጣ ለማሯሯጥ ስትሞክር ትንፋሽ አጥሯታል፡፡ ውብሸት የግማሽ ማራቶን ሯጮችን አቋም እና ብርታት አይቶ ቁጭት አድሮበታል፡፡ ለሁሉም መልካም ዜና አለ፡፡ የሀዋሳ ግማሽ ማራቶን በአመቱ ይመጣል፡፡       

More To Explore

10KM

የ2015 ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ ዘመቻ የታቀደለትን ገቢ አሰባስቦ ለሶስት በጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረከበ፡፡

በዘመቻው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ መንገዶች ተሰብስቧል፡፡ ታህሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም.፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በመተባበር የተለያዩ