የትውልድ ዘመን፡- ሚያዝያ 25/1987
የትውልድ ስፍራ፡- ኦሮሚያ ክልል ጉጂ
ቁመት፡- 1.62 ሜ.
ክብደት፡- 45 ኪ.ግ.
ማናጀር፡- ሁሴን ማኪ
ክለብ፡- ፌደራል ማረሚያ ቤቶች
ሰንበሬ ተፈሪ ወደሩጫው ዓለም የተቀላቀለችው በደቡብ ኢትዮጵያ ጉጂ ዞን በ2002 ዓ.ም. የአትሌት መልማዮች የምትማርበት ትምህር ቤት ድረስ መጥተው ምርጫ ባደረጉበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ስድስት ወንድም እና ሶስት እህቶች ያሏት ሰንበሬ በግብርና ስራ የሚተዳደሩት ወላጆቿ ስለሩጫ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ እና መሮጧንም ብዙም የሚደግፉት እንዳልነበሩ ትናገራለች፡፡ “ሩጫ ስጀምር ድጋፍ አገኝ የነበረው ከአስተማሪዎቼ ነበር” የምትለው ወጣት በመልማዮች ከመመረጧ በፊት የሩጫ ልምምድ የሚሰራም ሰው አይታ እንደማታውቅ እና ስለተመረጠች ብቻ ወደሩጫው እንደገባች ታስታውሳለች፡፡ “አክስቴ ሱሌ ታዋቂ አትሌት ብትሆንም እርሷ ወደከተማ ስትመጣ እኔ በጣም ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ ስለሯጭነቷ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም” በማለት ታክላለች፡፡ የዓለም ወጣቶች 5000ሜ. ሻምፒዮን እንዲሁም የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የ5000ሜ. እና 10,000ሜ. የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ሱሌ ኡቱራ አክስቷ የሆነችው ሰንበሬ ከቤት ወደትምህርት ቤት ስትሄድ እና ስትመጣ ወደ ሰባት ኪሎ ሜትር ያህል የሚርቀውን እና ዳገት ይበዛበት የነበረውን መንገድ በሩጫ ትሄድ እና ትመጣ የነበረ መሆኑ አሁን ውጤታማ ሯጭ ለመሆኗ የበኩሉን በጎ አስተዋፅኦ ሳያደርግላት እንዳልቀረም ታምናለች፡፡
በ2002 ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረገችው ውድድር በቦሬ ከተማ የተካሄደ የ6 ኪ.ሜ. የአገር አቋራጭ ውድድር ሲሆን ጉጂ ዞንን ወክላ የተፎካከረችበትን ይህን ውድድርም በአሸናፊነት ለመጨረስ ችላለች፡፡ በመቀጠል በዛው ዓመት አሰላ ላይ በተካሄደው የመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ላይ በተመሳሳይ በ6 ኪ.ሜ. የአገር አቋራጭ ውድድር ጉጂ ዞንን ወክላ ቀርባ ያሸነፈች ሲሆን ይህ ውጤቷም በዛው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ከተቋቋሙት 25 የአትሌቲክስ ክለቦች አንዱ በሆነው የአምቦ ክለብ ለመታቀፍ አብቅቷታል፡፡ ይህ አጋጣሚ ከመኖሪያ አካባቢዋ ለቃ ወደ አምቦ ከተማ በማቅናት ካምፕ እንድትገባ እና ትምህርቷን አቋርጣ ትኩረቷን ሙሉ በሙሉ በሩጫው ላይ እንድታደርግ ምክንያት ሆኗል፡፡
በ2003 ዓ.ም. አዳማ ላይ በተከናወነው የኦሮሚያ ውድድር ክለቧ አምቦን ወክላ በ1500ሜ. ለማሸነፍ መብቃቷም በዛው ዓመት በተከናወነው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ የኦሮሚያ ክልልን እንድትወክል ለመመረጥ አስችሏታል፡፡ በዛው ዓመት የኦሮሚያ ክልልን ወክላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት 40ኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ1500 ሜ. 4፡20.29 (dqE”ÝskNDÝ¥YKé skND) በሆነ ሰዓት አራተኛ የወጣች ሲሆን በዚህ አጋጣሚም ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተመርጣ በፈረንሳይ ሊል በተካሄደው የዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይ ለመጀመሪያ ግዜ ሀገሯን ወክላለች፡፡ በሊል በተካሄደው የዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይም በ1500ሜ. የብር ሜዳልያ ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡
ሰንበሬ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እንዴት እንደመጣች ስታስረዳ “ከዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና መልስ በ2003 መጨረሻ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች ክለብ የፈረምኩ ሲሆን በዚህ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ስመጣም ለስድስት ወር ያህል ሱሌ ጋር ነበር ያረፍኩት፡፡ ወደዚህ ከመጣች ብዙም ግንኙነት ስላልነበረን አክስቴ ሱሌ አድጌ የክለብ ተወዳዳሪ አትሌት ለመሆን በመብቃቴ በጣም ተገርማ ነበር፡፡ ወደዚህ ከመጣሁበት ግዜ ጀምሮ ከተማውን እንድላመድ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በማገዙ ረገድ ሱሌ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋልኛለች” ትላለች፡፡
2004 ዓ.ም. የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ክለብን ወክላ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተካሄደው 1ኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሻምፒዮና 4፡14.13 በሆነ ሰዓት እንዲሁም በ41ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4፡13.10 በሆነ ሰዓት
የ1500ሜ. አሸናፊ ለመሆን በቅታለች፡፡ በወጣቶች ውድድሩ ላይ ያስመዘገበችው ውጤት በዛው ዓመት ባርሴሎና ላይ በተደረገው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ሀገሯን ለመወከል እንድትመረጥ ያበቃት ሲሆን ወደ ባርሴሎና አቅንታም በ1500ሜ. የነሐስ ሜዳልያ ለማስገኘት በቅታለች፡፡
በ2005 ዓ.ም. መጋቢት ወር ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄደው 2ኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ሻምፒዮና ክለቧ ማረሚያ ቤቶችን ወክላ በ3000ሜ. የተወዳደረች ሲሆን በ9፡12.96 (dqE”ÝskNDÝ¥YKé skND) ሰዓት አንደኛ በመሆን አሸንፋለች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳየች የመጣችውን መሻሻል አጠናክራ የቀጠለችው ሰንበሬ ምንም እንኳ ጠንካራ የሚባሉት አትሌቶች የነበሩ ባይሆንም በዛው ዓመት አሰላ ላይ በተካሄደው 42ኛው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይም በወቅቱ የራሷ ምርጥ በሆነ 16፡20.99 (dqE”ÝskNDÝ¥YKé skND) ሰዓት የ5000ሜ. ሻምፒዮን ሆናለች፡፡ በ2005 በጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ላይም ክለቧን ወክላ ተሳትፋ የነበረ ሲሆን በወጣት ሴቶች 6 ኪ.ሜ. 8ኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
ሰንበሬ ከመም እና አገር አቋራጭ ውድድሮች በተጨማሪም በሀገር ውስጥ በተካሄዱ የጎዳና ላይ ውድድሮች ላይ ስኬታማ የሚባል የተሳትፎ ታሪክ አላት፡፡ በተለይም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚያካሂደው የሴቶች 5 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ውድድር በተከታታይ ለሶስት ዓመታት (የ2004፣ 2005 እና 2006 ዓ.ም.) አሸናፊ ስትሆን በ2004 የመጀመሪያውን ድሏን ያስመዘገበችውም ከዚያ በኋላ በ2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን ሻምፒዮን መሆን የቻለችውን እና በጎዳና ላይ ውድድር የከፍተኛ ልምድ ባለቤት የነበረችው ቲኪ ገላናን ጭምር በመቅደም ነበር፡፡
ከገጠራማው ጉጂ ተነስታ በቦሬ በኩል አልፋ አሰላ ላይ አብባ አምቦ ላይ ከጎመራች በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለዓለም አቀፍ ዕውቅና የበቃችው ሰንበሬ በዓለም አገር አቋራጭ፣ በዓለም ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያን ለመወከል የበቃች ሲሆን በ2015 ዓ.ም. በቻይና በተካሄዱት የጉያንግ የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዓለም አገር አቋራጭ እና የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ዓለም ሻምፒዮና ውድድሮች ላይም በአዋቂዎች 8 ኪ.ሜ. እና በ5000ሜ. የብር ሜዳልያ አሸናፊ መሆን ችላለች፡፡ ባለፈው ዓመት በብራዚል ሪዮ ደ ጃኔይሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የ5000ሜ. የፍፃሜ ተፎካካሪ የነበረችው የ22 ዓመቷ ሰንበሬ ከቀናት በኋላም በእንግሊዝ ለንደን በሚካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን ወክለው ለመወዳደር በመዘጋጀት ላይ ከሚገኙት አትሌቶች መካከል አንዷ ናት፡፡