እንጦጦ ፓርክ ፕሬዲተር ሩጫ – 6 ኛ ዙር ቅዳሜ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ይካሄዳል
ራእዬ አማን እና ሀብታሙ አበራ “ፕሬደተር” ተብለው ይሸለማሉ?
በየወሩ የሚካሄደው የእንጦጦ ፓርክ ፕሬዲተር ሩጫ ውድድር ለ6ኛ ጊዜ ነሐሴ 01 ቀን 2013 ይካሄዳል ፡፡
በተሳታፊዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅነት ያገኘው ይህ ውድድር ሙሉ በሙሉ ምዝገባውን በየነ መረብ ላይ ያደረገ ነው ፡፡ የመጀመሪያ ዙር ውድድር በ125 ተሳታፊዎች ከትራፊክ ነፃ በሆነው የተፈጥሮ ፓርክ ውስጥ ሲጀምር አሁን ከ250 በላይ ተመዝጋቢዎች አሉት፡፡ ባሳለፍነው ወር ውድድሩ 280 የጤና ሯጮችን አሳትፏል ፡፡
ውድድሩን ሦስት ጊዜ የሚያሸንፉ ተሳታፊዎች የውድድሩ “ፕሬደተር” ተብለው የብር ሰሃን ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ ነሃሴ 1 የሚካሄደው ውድድር ይህን ሽልማት የማግኘት እድል ያላቸውን ተሳታፊዎች ያሳትፋል፤
እስካሁን ድረስ በተደረጉት ተከታታይ ውድድሮች በሴቶች ምድብ ፈጣን ሰዓት የተመዘገበው 25 ደቂቃ ከ 41 ሰከንድ ሲሆን በወንዶች ምድብ ደግሞ 18 ደቂቃ ከ 18 ሰከንድ ነው።
የውድድሩ ሁለት ጊዜ አሸናፊ የሆነችው ተማሪ ራይዬ አማን “ቀደም ሲል የጤና ችግር ነበረብኝ በዚህም ምክንያት ነው ከአባቴ ጋር መሮጥ ጀመርኩት፤ አሁን ጤናማ ነኝ እና ሩጫን እወዳለሁ። ለወደፊቱ ስኬታማ አትሌት መሆን እፈልጋለሁ። ” በማለት ሩጫ እና ለውድድሩ ያላት ፍቅር ትገልፃለች ፡፡
ሁለት ጊዜ የወንዶቹን ውድድር ያሸነፈው ሀብታሙ አበራ ፀጉር አስተካካይ ሲሆን ስለ ዝግጅቱ እንዲህ ይላል-“ከዚህ ቀደም ቴኳንዶን እሠራ ነበር ነገር ግን በኮቪድ-19 ምክንያት ሁሉም የጤና ማዘውተሪያዎች ተዘግተው ስለነበር በራሴ መሮጥ ጀመርኩ። ከዚያም በእንጦጦ ለመጀመሪያ ጊዜ መወዳደር ተመዘገብኩ እስካሁን ሁለት ጊዜ አሸንፌያለሁ። አሁን በሁለት ቀን ልዮነት ሥልጠና እሰራለሁ። ”